የአውስትራሊያ መንግሥት የማይናማርን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ለዕገታ የታደረጉ ዜጎቹን ለመታደግ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።
መንግሥት በወርኃ ኖቬምበር በተካሄደው አገራዊ ምርጫ አሽንፎ ዳግም ለስልጣን በቅቶ ከነበረው የአንግ ሳን ሱ ቺ መንግሥት መከላት ጋር ተያይዞ ስልጣን ተቆጣጥሮ ያለው ወታደራዊ መንግሥት ዘብጥያ ላወረዳቸው አውስትራሊያውያን የቆንሱላ እገዛ እያደረገ መሆኑንም ገልጧል።
የአውስትራሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜሪዝ ፓይን ፖሊስ ጣቢያ ታግተው ያሉት አውስትራሊያዊው የአንግ ሳን ሱ ቺ የምጣኔ ሃብት አማካሪ ሾን ተርነል ጉዳይ ብርቱ ስጋት ያሳደረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ወታደራዊ ቡድኑ ዓርብ ፌብሪዋሪ 5 የኢንተርኔት አገልግሎት የዘጋ ቢሆንም ማይናማር ውስጥ የተቃውሞ ሰልፎች ግና ቀጥለዋል።
ያንጉን ከተማ ውስጥ በአሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ 'ወታደራዊ አምባገነንነትን እናወግዛለን' የሚሉ መፈክሮችን በመያዝና 'ድል ለዲሞክራሲ' የሚሉ ድምጾችን አሰምተዋል።
የኮቨድ-19 ክትባት - ምዕራብ አውስትራሊያ
የምዕራብ አውስትራሊያ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን ከፌብሪዋሪ 22 ጀምሮ ባሉት ቀናት ለነዋሪዎቹ መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ።
ፕሪሚየር ማርክ ማክጋዋንና የጤና ሚኒስትር ሮጀር ኩክ የክትባት ስርጭቱን አስመልክቶ ወሸባ ግብተው ላሉ፣ የዓለም አቀፍ ድንበሮች ሠራተኞችና የጤና ክብካቤ ሠራተኞች ቅድሚያ እንደሚያገኙ ገልጠዋል።
ምዕራብ አውስትራሊያ የተወሰኑ የፋይዘር ክትባቶችን ያገኘች ሲሆን፤ ተከታቢዎች ሁለተኛ ክትባታቸውን ከሶሶት ሳምንታት በኋላ እንደሚያገኙም ተነግሯል።
ክትባቶቹም በስድስት የጤና ግልጋሎት መስጫዎች፤
- በፐርዝ የሕጻናት ሆስፒታል፣
- በአልባኒ፣
- ሄድላንድ፣
- ካልጉሊ፣
- ጄራልድተንና
- ብሩም የጤና ካምፓሶች ይሰጣሉ።
አቶ ኩክ ክትባቶቹን አስመልክተው ሲናገሩ፤
"ክትባቱ ዝግጁ በሆነበት ወቅት ሁሉም ሰው እንዲከተብ አሳስባለሁ። ምዕራብ አውስትራሊያ ውስጥ የፋይዘር የመጀመሪያ ዙር ክትባቶች ፌብሪዋሪ 22 ግድም ይከፋፈላል" ብለዋል።

