አውስትራሊያ ውስጥ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ክትባት ከፌብሪዋሪ አጋማሽ እስከ ወሩ መጨረሻ ባሉት ቀናት መሰጠት ይጀመራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አረጋውያንና የጤና ክብካቤ ሠራተኞችን ጨምሮ አራት ሚሊየን አውስትራሊያውያን የኮቨድ-19 ክትባት ሊከተቡ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
የመፈወሻ ቁሳቁሶች አስተዳደር በዚህ ወር መጨረሻ የፋይዘር ክትባት ግብር ላይ እንዲውል ይሁንታን የሚሰጥ ሲሆን በመቀጠልም ለሌሎች ክትባቶች በተከታታይ ፈቃድ ይሰጣል።
አቶ ሞሪሰን ምንም እንኳ ክትባቶቹ መሰጠት ቢጀምሩም አውስትራሊያውያን ዓመቱን ሙሉ ተገቢው የኮቨድ-19 ጥናቃቄዎችን በማድረግ እንዲቀጠሉ አሳስበዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ
የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ በፕሬዚደንት ትራሞ ደጋፊዎች ከተናወጠ በኋላ ለ46ኛው ተመራጭ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የምስክር ወረቀት ለመስጠት ዳግም ታድሟል።
አመፅ በተቀላቀለበት የተቃውሞ ተግባር ሳቢያ እስካሁን የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተገልጧል። ከ50 እስከ 52 የሚደርሱ የጆ ባይደንን ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ ጥረት ያደረጉ ተቃዋሚዎች ለእስር ተዳርገዋል።
የዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ከንቲባ ከምሽቱ 6:00 pm ጀምሮ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ጥለዋል።
የዲሞክራቶች የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት መሪ ቻክ ሹመር ምንም እንኳ የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ በነውጥ ቢናጋም "ዲሞክራሲ ያሸነፋል" ብለዋል።
አክለውም፤
"ጃኑዋሪ 6 በአሜሪካ የቅርብ ታሪክ ውስጥ ከጨለማዎቹ ቀናት አንዱ ሆኖ በታሪክ ይሰፍራል። የዛሬው ሁነት በድንገት የሆነ አይደለም። ወደ አገሪቱ መዲና ያመጣቸው የፕሬዚደንቱ የሴራ ቃለ ነቢብ ነው። በእሳቸው ቃላት፣ ቅጥፈቶች ባይነሳሱ ኖሮ የዛሬው ሁነት በእርግጥ፣ በእርግጥ ባልተፈጸመ ነበር" ሲሉ ብርቱ ትችታቸውን ፕሬዚደንት ትራምፕ ላይ ሰንዝረዋል።
የአውስትራሊያ ፖለቲከኞች ከቀረው ዓለም መሪዎችና ፖለቲከኞች ጋር ታክለው የአመፅ ክስተቱን አውግዘዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜሪዝ ፓይን የአመፅ ተግባሩን በማውገዝ ሰላማዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር እንዲካሄድ አሳስበዋል።
የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንቶኒ አልባኒዚ የዶናልድ ትራምፕ ቃላትና ግብሮች ለዚህ ክስተት መከሰት አበረታች መሆን ምንም ጥርጥር የለውም፡፤ ይህ እውነተኛ ስጋት ነው። የዲሞክራሲ ደጋፊዎች በሙሉ ይህን አስመክተው ሊናገሩ ይገባል" ሲሉ ትችትና ጥሪ አቅርበዋል።

