የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በምሥራቃዊ ባሕረ ሰላጤ የባሕር ሰርጓጅ መርከብ ብሔራዊ አቅም ግንባታን አስመልክቶ ዛሬ ሰኞ ማርች 7 የነደፉትን ዕቅድ ያስታውቃሉ።
ለባሕር ሰርጓጅ መርከቡ ሥራ ማከናወኛ ኬምብላ ወደብ፣ ብሪስበንና ኒውካስል በተመራጭ ሥፍራነት ስማቸው ተጠቅሷል።
አቶ ሞሪሰን አውስትራሊያን ገጥሟት ካለው የፀጥታ ሁኔታ ጋር አያይዘው የምዕራባውያን ዲሞክራሲ አገራት በጋራ የጨቋኞችን የአመፅ እርምጃ የመቋቋም አስፈላጊነት አመላክተዋል።
በዛሬው ዕለት በሎዊ መካነ ጥናት በሚያደርጉት ንግግር የዩክሬይንን ወረራ አንስተው እንስተው እንደሚናገሩ ይጠበቃል።
የፆታ የተመረኮዘ ክፍያ ክፍተት
በአንድ የጡረታ አበል ድርጅት አማካይነት በተካሔደ ምርምር ግማሽ ያህል አውስትራሊያውያን የፌዴራል መንግሥቱ የሴቶችን የክፍያ ክፍተት የማጥበብ ኃላፊነት እንዳለበት የሚያምኑ መሆኑን ገለጠ።
ከማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በፊት ይፋ የሆነው የጥናቱ ግኝት እንዳመለከተው 90 ፐርሰንት ሴቶች የክፍያ ክፍተቱ ፍትሐዊ አለመሆኑን ያምናሉ።
በወንዶችና ሴቶች መካከል ያለው የክፍያ ክፍተት ላለፉት አሠርት ዓመታት ረብ ያለው መሻሻል ያልታየበት በመሆኑ በወንዶችና ሴቶች ሳምንታዊ የሙሉ ቀን ሠራተኞች ክፍያ መካከል 22.8 ፐርሰንት ልዩነት አለ።
የምርምር ውጤቱ ልጆች ወልደው ልጆቻቸውን ለመከባከብ ከሥራ በሚለዩት የገቢ ምንጭ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ መሆኑን ጠቁሟል።
ዩክሬይን ኑክሊየር
የተባበሩት መንግሥታት የኑክሊየር ተቆጣጣሪ የዩክሬይን ኑክሊየር ጣቢያ ባለፈው ሳምንት በሩስያ ቁጥጥር ስር ከወደቀ ወዲህ በሩስያውያን ተቆጣጣሪነትና በዩክሬናውያን ሠራተኛነት እየተካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
ሆኖም የሩስያ ጦር የዛፖሪዝህያ ኑክሊየር ጣቢያ ሞባይል አውታረ መረብና ኢንተርኔት እንዲቋረጥ ማድረጋቸውን አስመልክቶ የዓለም አቀፍ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ዋና ኃላፊ ስጋታቸውን ገልጠዋል።
ተመድ የዩክሬይን ግጭት ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ከ350 በላይ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 1.5 ሚሊየን ለስደት መዳረጋቸውን አስታውቋል።
ኦዴሳ ዩክሬይን
የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቫሎድሚር ዜሌንስኪ የሩስያ ጦር በጥቁር ባሕር ሰላጤ የምትገኘውን የኦዴሳ ከተማን ለማጥቃት መሰናዶ እያደረገ መሆኑን ጠቆሙ።
አቶ ዜሌንስኪ የሩስያ ጦር ጥቃቱን ከፈፀመ የጦር ወንጀል እንደሚፈፅም አሳስበዋል።
የዩክሬይን ፕሬዚደንት ሩስያውያን ከ20 ዓመት በላይ ሩስያን በመሩት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ተቃውሞ እንዲነሳ ጥሪ አቅርበዋል።
ዩክሬይን ሩስያ
የሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬይን ዘመቻቸው ባቀዱት መሠረት በስኬት እየተካሔደ መሆኑን ዳግም ገለጡ።
ፕሬዚደንቱ ይህን የተናገሩት የተኩስ ማቆም እንዲካሔድ ለማግባባት ጥረት ላይ ካሉት የቱርኩ ፕሬዚደንት ሬትቼፕ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር በስልክ በተነጋገሩበት ወቅት ነው።
አቶ ፑቲን ዩክሬይን ፍልሚያዋን እስካላቆመችና ለምዕራባውያን እያደረገች ያለችው የማዕቀብ ጥሪ እስካልተገታች ድረስ ሩስያ ጥቃቷን እንደምትቀጥል ተናግረዋል።
አቶ ፑቲን ለዳግም ፕሬዚዳናዊ ምርጫ ተወዳዳሪነታቸውን ይፋ ካደረጉት የፈረንሳዩ ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ከሁለት ሰዓታት የበለጠ በስልክ ተወያይተዋል።
ጎርፍ ኒው ሳውዝ ዌይልስ
የሜትሮሎጂ ቢሮ በምሥራቃዊ ኒው ሳውዝ ዌይልስ ተጨማሪ ከባድ ዝናብ እንደሚጥል አመላከተ።
በጎርፍ የተጎዱ ከተሞች ቀዬዎቻቸውን የማፅዳት ዘመቻ ጀምረዋል።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለተጎጂዎች አላቀረበም በሚል ብርቱ ትችት እየደረሰበት ሲሆን፤ መንግሥት በበኩሉ አስቸኳይ እርዳታ ለማድረስ ሁኔታዎች አዋኪ እንደነበሩ ገልጧል።
ፕሪሚየር ዶሚኒክ ፔሮቴይ ወደፊት የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመከላከል የተሻለ ዕቅድ መንደፍ ግድ እንደሚል ከሊዝሞር ለ ABC አስታውቀዋል።
ለአገር መከላከያ 5000 ጦር እርዳታ ጠይቀው አብዛኞቹ ባለፉት ሁለት ቀናት ጉዳት ወደ ደርሰባቸው አካባቢዎች መድረሳቸውን አክለው ገልጠዋል።
አንድ በጎርፍ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ የ60 ዓመት ሰውን ጨምሮ ኩዊንስላንድ ውስጥ በጎርፍ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር 12 ደርሷል።

