የአውስትራሊያ ፌዴራል መንግሥት ሁሉንም የሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ምክረ ሃሳቦች እንደሚቀበል አስታወቀ

*** የአውስትራሊያ ደንጋጊዎች የአስትራዜኒካ ቫይረስ ክትባትን ከደም መርጋት ጋር መያያዝ አስመልክቶ ክለሳ ያደርጋሉ

SBS Amharic

Source: SBS Amharic

የፌዴራል መንግሥቱ የሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳ ምክረ ሃሳቦችን በከፊል፣ በመርህ ደረጃ ወይም ሙሉ በሙሉ እንደሚቀበል አስታወቀ።

መንግሥት በዛሬው ዕለት እቀበለዋላቸዋለሁ ያላቸው 55 'ከበሬታ በሥራ ላይ' ሪፖርት ምክረ ሃሳቦች በጾታ መድልኦ ኮሚሽነር ኬት ጄንኪንስ ቀርበውለት የነበረው ባለፈው ዓመት ወርኃ ጃኑዋሪ ነው።    

ምክረ ሃሳቦቹም በሥራ ሥፍራ ወሲባዊ ትንኮሳ ረቂቅ ድንጋጌነት ተቀርፀው በዚህ ዓመት ለፓርላማ እንደሚቀርቡ ጠቅላይ ዐቃቤ ህጓ ሚካሊያ ካሽ ተናግረዋል።

ድንጋጌውም ከሥራ እስከማባረር የሚያደርስ አቅም የሚኖረው እንደሆነ ገልጠዋል።

አያይዘውም፤

"ወሲባዊ ትንኮሳ በኅብረተሰባችን ውስጥ በየትኛውም ሥፍራ ተቀባይነት የለውም። የከበሬታ ፍኖተ ካርታ ግብረ ምላሻችን ትርጉም ያለው፣ በመላው አገሪቱ እንዲሰፍን ለማስቻልና ለሁሉም አውስትራሊያውያን የሥራ ቦታ ደህንነት የተመላበት ለማድረግ ነው" ብለዋል። 

ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት አስመልክቶ መረጃ ወይም ድጋፍ ካሹ  በ1-800 RESPECT ወይም 1800 737 732 መደወል ይችላሉ።

                                                

 ክትባት 

 የፌዴራል መንግሥቱ የአውስትራሊያ ሕክምናና ክትባት ደረጃ መዳቢዎች ከአስትራዜኒካ የኮሮናቫይረስ ክትባት ጋር ተያይዞ ተከስተው ያሉትን ውስን የደም መርጋት ክስተቶች በተመለከተ የአውሮፓ ሕክምና ኤጄንሲን (አሕኤ) ግኝቶች ተመርኩዘው ክለሳ እንዲያደርጉ ጠየቀ።

 ኢሕጄ በአውሮፓና እንግሊዝ ክትባቱን የተከተቡትንና የደም መርጋት የገጠማቸውን በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ጉዳይ መርምሯል።

በምርምር ግኝቱም አብዛኛዎቹ የደም መርጋት ክስተቶች የተከሰቱት ዕድሜያቸው ከ60 በታች የሆኑ ሴቶች ክትባቱን በተከተቡ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ነው። 

ሆኖም በቅርቡ የተገኙ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በተለየ መልኩ ተጋላጭ የሆኑ ክስተቶች አልተገኙም።  

ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን ይህን ተመርኩዞ የአውስትራሊያ ክትባት ፕሮግራም ላይ የባለ ሙያ ምክሮችን እስከሚሰሙ ድረስ የሚደረጉ ለውጦች እንደሌሉ ጠቁመዋል።

 ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በመላው አውሮፓ የአሕኤን ግኝቶች ተመርኩዘው በአስትራዜኒካ የኮሮናቫይረስ ክትባት አሰጣጥ ላይ የዕድሜ መመዘኛዎች ለውጦችን አድርገዋል።

የእንግሊዝ ጤና ባለ ስልጣናት እንደአመቺነቱ ዕድሜያቸው ከ30 በታች የሆኑ ጎልማሶች ተለዋጭ ክትባት እንዲከተቡ ይሁንታቸውን ሰጥተዋል።

የጀርመን ባለ ስልጣናት ዕድሜያቸው ከ60 በታች የሆኑና የመጀመሪያ አስትራዜኒካ ክትባትን የተከተቡ ሰዎች ለሁለተኛ ጊዜ የሚከተቡት ክትባት የተለየ እንዲሆን ወስነዋል።

የስፔይን ጤና ሚኒስትር ካሮሊና ዳሪያስ የአስትራዜኒካ ክትባት የሚሰጠው ዕድሚያቸው ከ60 በላይ ለሆኑ ሰዎች ብቻ መሆኑን ገልጠዋል።     

 በሌላ በኩል የቪክቶሪያ መንግሥት 300,000 የኮሮናቫይረስ ክትባቶችን እስከ ወርኃ ሜይ አጋማሽ ለመከተብ ዕቅድ ይዟል። 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 


2 min read

Published

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now