ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመደመር መጽሐሃፍ ሽያጭ የተገኘውን ከ110 ሚሊየን ብር በላይ ለትምህርት ቤቶች ማሰሪያ አስረከቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ የተገኘውን 110 ሚሊየን 671 ሺህ ብር በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ለሚገነቡ ትምህርት ቤቶች ሥራ ማከናወኛ ያስረከቡ ሲሆን ገንዘቡን ቀዳማዊት እመቤት ወይዘሮ ዝናሽ ታያቸው ተቀብለዋል፡፡
የወ/ሮ ዝናሽ ጽሕፈት ቤት በአገር አቀፍ ደረጃ እያስገነባቸው ካሉት 20 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰባቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቀዋል።
ቀሪዎቹ 13 በግንባታ ላይ ያሉት ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው ከ90 በመቶ በላይ የተጠናቀቀ ሲሆን በሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ግልጋሎታቸውን መስጠት ይጀምራሉ ተብሎ እንደሚጠብቅ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ቪክቶሪያ ውስጥ ዛሬ ዕለተ ቅዳሜ 466 ሰዎች በኮሮናቫይረስ ሲጠቁ 12 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ አንዱ በ30ዎቹ፣ ሁለት ወንዶች በ70ዎቹ፣ ሶስት ሴቶች በ80ዎቹ፣ አራት ሴቶች በ90ዎቹ ዕድሜ የነበሩ ሲሆኑ፤ ስድስቱ የአረጋውያን መጦሪያ ቤቶች ነዋሪዎች የነበሩ መሆናቸውን ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ አስታውቀዋል።
እስከ ዛሬዋ ቅዳሜ 636 የኮሮናቫይረስ ሕሙማን በቪክቶሪያ ሆስፒታል ተኝተው ሕክምና እየተከታተሉ ሲሆን፤ 44ቱ በፅኑ ሕመምተኞች ክፍል፣ 29ኙ በመተንፈሻ መሳሪያዎች እየተረዱ ይገኛሉ።
ቪክቶሪያ ላለፉት 34 ቀናት በተከታታይ ባለ ሶስት ዲጂት በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር አስመዝግባለች።
ምንም እንኳ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር በየዕለቱ በ400 እና 500 መካከል ቢሆንም የቁጥሮቹ መርጋት መልካም መሆኑን የቪክቶሪያ ዋና የሕክምና ኃላፊ ፕሮፌሰር ብሬድ ሳተን ገልጠዋል።
አያይዘውም በደረጃ ሶስት የኮሮናቫይረስ ወረርሽ ገደቦች ሳቢያ ከ20 ሺህ በላይ ቪክቶሪያውያን በቫይረሱ እንዳይጠቁ መገደብ የተቻለ መሆኑንና የደረጃ አራት ገደብም በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ከፍ ያለ ለውጥ እንደሚያስገኝ ያላቸውን አመኔታ አስታውቀዋል።
እስከ ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት ድረስ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ሲጋራና ከረሜላ ለመግዛት የወጣን አንድ ግለሰብ አክሎ 200 ቪክቶሪያውያን በሰዓት ዕላፊ ገደብ ጥሰት ለቅጣት በቅተዋል።
ግለሰቡ የተያዘው ከእኩለ ለሊት በኋላ 1am ላይ በአንድ የነዳጅ መሸጫ አጠገብ ሲሆን፤ ከ8pm - 5am የተጣለውን የሰዓት ዕላፊ ገደብን በመተላለፍ $1652 እንዲሁም ጭምብል ባለማጥለቅ የ$200 መቀጮ ተጥሎበታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ በዛሬው ዕለት ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ ዘጠኝ ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሲሆን፤ በጥቅሉ 3,662 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

