አዲሱ የአልባኒዚ መንግሥት የብሔራዊ ፀረ - ሙስና ኮሚሽን ድንጋጌ በዚህ ዓመት መጨረሻ ፀድቆ በ2023 አጋማሽ ላይ ሥራውን እንደሚጀምር ይጠበቃል።
አዲሱ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማርክ ድሬይፈዝ የሌበር ፓርቲ በአገር አቀፍ ምርጫ ዘመቻ ወቅት የገባውን ሁነኛ ቃል ዕውን ለማድረግ በዲፓርትመንታቸው ውስጥ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም አድርገዋል።
ሌበር የኮሚሽኑንን ተግባራትና ስልጣን አስመልክቶ ከግል ተመራጭ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ይመክራል፤ እንዲሁም ከክፍለ አገራት ፀረ - ሙስና ኮሚሽኖች የአፈፃፃም መርሃ ግብር የሚወስዳቸውንም ይመለከታል።
አቶ ድሬይፈዝ ግብር ላይ ሊያውሉት አስበውት ስላለው ኮሚሽን ለ A-B-C ሲናገሩ፤
"ኮሚሽኑ ነፃና ገለልተኛ ይሆናል። ብርቱ ስልጣን ያለው ይሆናል። የሮያል ኮሚሽን ስልጣኖች ይኖሩታል። ብርቱና መዋቅራዊ ሙስናን ይመረምራል። ከተለያዩ ምንጮች ጥቆማዎችን ይቀበላል፤ ምስጢራዊነታቸው የተጠበቀ ይሆናል። በይፋ የሙስና ምርመራ ስሚዎችን ያካሂዳል። እነዚህ ሁሉ በጣሙን አስፈላጊ ናቸው፤ ካለፈው መንግሥት ረቂቅ ድንጋጌም የተለየ ነው" ብለዋል።
ዩክሬይን - የዓለም ባንክ
የዓለም ባንክ ተጨማሪ $1.5 ቢሊየን ለዩክሬይን ሰጠ።
ድጎማው ለመንግሥትና ማኅበራዊ ሠራተኞች ደመወዝ ክፍያ የሚውል ይሆናል።
ባንኩ እስካሁን ለዩክሬይን ከ $4 ቢሊየን በላይ ድጎማ አድረጓል።
የልማት አበዳሪው ባንክ ከተለያዩ አገራት ለጋሾች ጋር በመተባበር የደቀቀውን የዩክሬይን ምጣኔ ሃብት ለመታደግ፣ የጤና፣ የትምህርትና ማኅበራዊ ደኅንነት ለኡክሬናውያን ተደራሽነት እንዲሆኑ እየሠራ መሆኑን ገልጧል።

