ኢሰመኮ በወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ታስረው ያሉ የምክር ቤት አባላትንና ጋዜጠኞችን መጎብኘቱን ገለጠ

የጎንደር ሰዓት ዕላፊ ገደብ በአንድ ሰዓት ተሻሻለ

Dr Daniel Bekele.jpg

Dr Daniel Bekele, Chief Commissioner of the Ethiopia Human Rights Commission (EHRC). Credit: Anadolu Agency/Anadolu Agency via Getty Images

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዋሽ አርባ በሚገኘው የምዕራብ ዕዝ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በእሥር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን መጎብኘቱን ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 27 ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

አምስት አባላትን ያቀፈው የኢሰመኮ ጎብኚ ቡድን የተመራው በዋና ኮሚሽነሩ ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ሲሆን ጉብኝቱን ያካሔደው ነሐሴ 26 ነው።

በወታደራዊ ማሰልጠኛው በእሥር ላይ ሆነው ያገኛቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ምክር ቤት አባል አቶ ዮሐንስ ቧያለውና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ዶ/ር ካሳ ተሻገር ሲሆኑ፤ ከብዙኅን መገናኛ አባላት ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረው፣ አባይ ዘውዱ፣ እና ቴዎድሮስ ዘርፉ፤ እንዲሁም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ አቶ በለጠ ጌትነት፤ እና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በኃላፊነት ይሠሩ የነበሩት አቶ ከፋለ እሱባለውን ጨምሮ በአጠቃላይ 53 ወንድ እስረኞች መሆናቸው ተመልክቷል።

ግለሰቦቹ ከአዲስ አበባ ከተማና ከአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ሥፍራዎች ተይዘው ከነሐሴ 15 ቀን እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ጊዜያዊ/መደበኛ ያልሆነ ማቆያ ጣቢያ የተወሰዱ መሆናቸውም ተጠቅሷል፡፡

ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹንና የፖሊስ ባለስልጣናትን በተናጠል ያነጋገረ ሲሆን፤ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛው በእሥር እንዲቆዩ የተደረጉትም አዲስ አበባ የሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ማቆያ ጣቢያ ላይ ከፍተኛ መጣበብ በመፈጠሩ ሳቢያ እንደሆን የተነገረው መሆኑን አስታውቋል።

ኮሚሽኑ፤ ከታሳሪዎቹ ውስጥ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አቶ ዮሐንስ ቧያለውን ጨምሮ ሕመምተኛ እሥረኞች ወደ አዲስ አበባ ለሕክምና ተወስደው መመለሳቸውን እንደተረዳ አመልክቶ፤ እሥረኞች ቤተሰቦቻቸውን በስልክ ለማነጋገር እንዲፈቀድላቸው መጠየቃቸውን አመልክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ኮሚሽኑ አብዛኛዎቹ ታሳሪዎች ብሔራቸው አማራ፣ እምነታቸው ኦርቶዶክስ ክርስቲያን መሆኑንና ለእስር የተዳረጉት በብሔር ማንነታቸው ብቻ መሆኑን እንደሚያምኑ፣ ከፊሎቹ በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በተያዙበትና ቤታቸው በተበረበረበት ወቅት በራሳቸውና በቤተሰብ አባል ላይ ድብደባ፣ ብሔር ተኮር ስድብ፣ ማጉላላት፣ ዛቻና ማስፈራራት እንደደረሰባቸው ሆኖም በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር ከሆኑ በኋላ የተፈጸመ ድብደባ ወይም አካላዊ ጥቃት አለመኖሩን፣ ከፊሎቹ በተለይም ከአማራ ክልል ተይዘው የመጡ ሰዎች ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው የት እንዳሉ እንኳን እንደማያውቁ የተረዳ መሆኑን በሪፖርቱ ገልጧል።

አክሎም፤ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ጋር በተያያዘ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ፤ በአማራ ክልል ደብረ ታቦር፣ ባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞችን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች፤ በኦሮሚያ ክልል በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በገላን እና በሸገር እንዲሁም ሌሎች ከተሞች፣ መደበኛ ያልሆኑ ቦታዎች ተይዘው ከነበሩት ውስጥ ከፊሎቹ የተለቀቁ መሆናቸውን እንደተረዳ አስታውቋል።

በሌላም በኩል፤ ኢሰመኮ ጋዜጣዊ መግለጫን ይፋ እስካደረገበት ጊዜ ድረስ የኤርትራ ፍልሰተኞችን ጨምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን ጉዳዮች ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ገልጧል።

መግለጫው በማጠቃለያው "ኢሰመኮ እስከ አሁን ስላደረገው ክትትል፣ ግኝቶች፣ ተግዳሮት እና ምክረ ሐሳቦች ነሐሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ ጋር የተወያየ ሲሆን፤ ስለ አጠቃላይ ሁኔታው፣ የሰብአዊ መብቶች አከባበርና ዘላቂ ሰላማዊ መፍትሔ ሐሳቦች ከልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይትና ምክክር የሚቀጥል መሆኑን" ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መግለጣቸውን አስታውቋል።

ጎንደር

በአማራ ክልል በተላለፈው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሳቢያ እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ተጥሎ የነበረው ሰዓት ዕላፊ ከነሐሴ 27 አንስቶ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት እንዲራዘም መወሰኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።

ለሰዓት ዕላፊው መሻሻል አስባቡ አንፃራዊ የፀጥታ መሻሻል መታየት መሆኑን ረዳት ኮሚሽነር አየልኝ ታክሎ ገልጠዋል።





 










Share

Published

Updated

By Kassahun Seboqa Negewo
Source: SBS

Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service