የጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አገር አቀፍ ምርጫን ለሜይ 21 መጥራት ተከትሎ የተቃዋሚ ቡድን መሪ አንቶኒ አልባኒዚ ለአውስትራሊያና አውስትራሊያውያን ያላቸውን ርዕይ ዛሬ ከቀትር በኋላ አመላክተዋል።
አቶ አልባኒዚ አውስትራሊያውያንን ዳግም ወደ አንድነት እንደሚያመጡና የተሻለ መፃኢ ዕድል እንደሚፈጥሩ አስገንዝበዋል።
ያለ አባት በእናት ብቻ የመንግሥት ቤት ውስጥ በችግር ያደጉ በመሆናቸው ለአውስትራሊያውያን የተሻለ ሕይወት ለመፍጠር እንደሚታትሩ ተናግረዋል።
አያይዘውም፤ የሌበር ፓርቲ የኑሮ ውድነትን የሚያቀልሉ ዕቅዶች እንዳሉት፣ በአነስተኛ አቅም የሚሠሩ ቤቶችን እንደሚገነባ፣ የአረጋውያን ክብካቤ ቀውስንና የብሔራዊ ብሮድባንድ አውታረ መረብ እክሎችን እንደሚከላ አመላክተዋል።
አውስትራሊያውያን በሜይ 21ዱ ምርጫ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ካበቋቸውም በአክብሮት እንደሚያገለግሉ፣ እምነት አጥቶ ያለውን የፖለቲካ ሥር ዓት እንደሚያቃኑና ብርቱ የፀረ መስና ኮሚሽን እንደሚያቆሙ ተናግረዋል።
ከአቶ አልባኒዚ ቀደም ሲልም የአገራዊ ምርጫውን ቀን ለሜይ 21 የቆረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አውስትራሊያውያን ፖለቲካ የሰለቻቸው እንደሆነና ይልቁንም በዚህ ምርጫ መፃኢው ጊዜ በጣሙን ጠቃሚ እንደሆነ አሳስበዋል።
አቶ ሞሪሰን ምርጫው አውስትራሊያውያን ባለፉት አዋኪ ሶስት ዓመታት ከተፈተነ መንግሥትና ፈተና ካልገጠመው የተቃዋሚ ቡድን የሚመርጡበት መሆኑን አመላክተዋል።

