62 ተሳፋሪዎችን ጭኖ ከጃካርታ እምብዛም ሳይርቅ የተከሰከሰው የኢንዶኔዥያ ቦይንግ 737 መንገደኞች አስከሬኖችና የአውሮፕላኑ ቁርጥራጭ የብረት አካላት ዛሬ እሑድ ከቀትር በኋላ ተገኝቷል።
ከ62ቱ ተሳፋሪዎች መካከል 10ሩ ሕጻናት ሲሆኑ ሁሉም ኢንዶኔዥያውያን ናቸው።
የስሪዊጃያ አየር መንገድ 737-500 የተከሰከሰው ቅዳሜ ከቀትር በኋላ ከመዲናይቱ ጃካርታ ሶካርኖ-ሃታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አኮብኩቦ በረራ ከጀመረ አሥር ደቂቃዎች በኋላ ነው።
በባለ ስልጣናት በኩል እስካሁን እስካሁን በሕይወት የተረፉ ሰዎች ካሉ በሚል የፍለጋ ተግባራት ላይ ከማተኮር በስተቀር ለአደጋው መንሰኤ ይህ ነው የሚል ምክንያት በይፋ አልተሰጠም።
የጃካርታ ፖሊስ ቃል አቀባይ ዩስሪ ዩኑስ "አንድ የመንገደኛ ዕቃዎችንና ሌላ የአስከሬን አካላትን የያዙ ሁለት ከረጢቶችን" ተረክበናል ብለዋል።
የስሪዊጃያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር SJ182 ከጃካርታ ተነስቶ የ90 ደቃኢቃ በረራውን አቅንቶ የነበረው የኢንዶኔዥያ አካል ወደ ሆነችው ቦርኒዮ ደሴት ነበር።

ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ስለ ቤተሰቦቻቸው ሁኔታ ለማወቅ ፖንቲያናክ አውሮፕላን ማረፊያ ይጠባበቁ ከነበሩት መካከል ያማን ዛይ እያነቡ ሲናገሩ "ከተሳፋሪዎቹ ውስጥ አራቱ የኔ ቤተሰቦች ናቸው። ሚስቴና ሶስት ልጆቼ። ሚስቴ ዛሬ የሕጻኑን ልጃችንን ፎቶግራፍ ልካልኝ ነበር… እንዲህ ባለ ሁነት ልቤ እንደምን ተሰንጥቆ አይበጫጨቅም?" ሲሉ በኃዘን ተመልተው ተናግረዋል።


