የአውስትራሊያ መከላከያ ኃይል በ2040 ቋሚ 80,000 የመከላካያ አባላትን በማከል በ30 ፐርሰንት ከፍ ሊል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በሚቀጥሉት ሁለት አሠርት ዓመታት በአጠቃላይ 101,000 ቋሚ አባላት ተጨማሪ በመሆን መከላከያውን እንደሚያጠናክሩት ተናግረዋል።
የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በመመልመልና ወደ ቋሚ አባልነት ለማብቃት 38 ቢሊየን ዶላርስ ከ2024 እስከ 2040 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ወጪ እንደሚሆንም ተገልጧል።
በሌላም በኩል የተቃዋሚ ቡድን ሌበር ፓርቲ መሪ አንቶኒ አልበኒዚ ዛሬ በሎዊ መካነ ጥናት በሚያደርጉት ቁልፍ የውጭ ፖሊሲ ንግግር ሌበር የዘንድሮውን ምርጫ ካሸነፈ የመከላከያ በጀት እስካሁን ካለው ከአውስትራሊያ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢ ሁለት ፐርሰንት በጀት ከፍ እንደሚል ይናገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የነዳጅ ዋጋ
የሩስያና ዩክሬይን ጦርነት በሩስያ ላይ ከተጣሉት ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች ጋር ተያይዞ የነዳጅ ዋጋ ከወዲሁ ማሻቀብ ጀምሯል።
አውስትራሊያ ውስጥ ፐርዝ፣ ሆባርት፣ ዳርዊንና አደላይድ የነዳጅ ዋጋ በሊትር ከሁለት ዶላር ያለፈ ሲሆን፤ ሲድኒና ሜልበርን በሊትር ከ$1.80 ከፍ ብሏል።
የመስኩ ተጠባባቢ የሆኑት ቪቬክ ደሃር እንዳሉት ሉላዊ ነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ ምናልባትም ከሩስያና ዩክሬይን ጦርነት በኋላም ተፅዕኖው ሊቀጥል እንደሚችል ግምት አሳድረዋል። እንደ ደሃር አባባል ከሆነ አውስትራሊያ የአንድ ሊትር ነዳጅ ዋጋ ከ$2.40 እስከ $2.45 ሊንር ይችላል።
ጎርፍ - የአየር ንብረት ለውጥ
የአየር ንብረት ለውጥ ምክር ቤት የምርምር ውጤት እንዳመለከተው የአውስትራሊያ ምሥራቅ ባሕረ ሰላጤ ላይ የተከሰተው የጎርፍ መጠን በአውስትራያ ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።
በአየር ንብረት ለውጥ ምክር ቤቱ ሪፖርት መሠረት ብሪስበን በዓመት ከምታገኘው የዝናብ መጠን ውስጥ 80 ፐርሰንቱን በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ አግኝታለች።
ከ 1,450 ቢሊየን ሊትር በሶስት እጥፍ የሲድኒ ወደብን ሊሞላ የሚችል ውኃ በሶስት ቀናት ውስጥ ብሪስበን ወንዝን ተቀላቅሎ ፈስሷል።
ኒው ሳውዝ ዌይልስንና ኩዊንስላንድ ውስጥ ለተጎጂዎች ወጪ የሚሆን የኢንሹራንስ ሽፋን ክፍያ በአሁኑ ወቅት $1.45 ቢሊየን የደረሰ ሲሆን በቅርቡ $2 ቢሊየን ለማለፍ ተቃርቧል።
የምክር ቤቱ ተወካይ ዊል ስቴፈን በእያንዳንዱ የሉላዊ አንድ ዲግሪ የሙቀት መጠን መጨመር እንዲህ ያሉ ክስተቶች በእጥፍ እንደሚጨምሩ መገመት እንደሚቻል አመላክተዋል።

