ለሜይ 21 ቀን ተቆርጦለት ትናንት የተጠራውን አገራዊ ምርጫ ተከትሎ ዛሬ ሰኞ ኤፕሪል 11 የምረጡኝ ዘመቻ በይፋ ተጀምሯል።
ከወዲሁም በዋነኛ ፓርቲዎቹ በኩል የበርካታ ሚሊየን ዶላሮች የምርጫ ቃል ኪዳኖች እየተሰጡ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የምርጫ ዘመቻቸውን እያካሄዱ ከነበረበት ኖውራ ገጠራማ ከተማ ለመንገድ ሥራ ማሻሻያ የሚውል $40 ሚሊየን ዶላርስ ቃል ሲገቡ፤ የተቃዋሚ ቡድን መሪው አንቶኒ አልባኒዚ ከሎንሴስተን ታዝማኒያ መስማት ለተሳናቸው ሕፃናት ክብካቤ የሚውል የ$1.5 ሚሊየን ዶላር ድጎማ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።
የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች
አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ዎች ሰሞኑን ባወጡት የሪፖርት ግኝቶቻቸው የአማራ ክልል ታጣቂዎች በትግራይ ክልል ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ የዘር ማፅዳትን ጨምሮ ወንጀሎች መፈፀማቸውን አመላክተዋል።
ድርጅቶቹ ምንም እንኳ የሪፖርታቸው ትኩረት ባይሆንም በትግራይ ታጣቂ ኃይሎች የተፈፀሙ የአመፅ እርምጃዎችንም ጠቅሰዋል።
ሪፖርቱ 427 የጥቃት ሰለባዎችን፣ የቤተሰብ አባላትና የዓይን እማኞችን የምስክርነት ቃሎች ያሰባሰበ መሆኑም ተጠቁሟል።
የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶቹ ሪፖርት የአማራ ታጣቂ ኃይሎች ጭፍጨፋ መፈፀማቸውን፣ ሕጋዊ ያልሆነ እሥራት ማካሔዳቸውን፣ እገታ፣ የቁም ከብቶች ግድያ፣ ስርቆት፣ ሰቆቃና የትግርኛ ቋንቋ ንግግር ግደባ እርምጃዎችን መፈፀማቸውን አመልክቷል።
ሪፖርቱ የአፍሪካ ኅብረትና የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበርና የጦር መሣሪያ እገዳ እርምጃዎችን እንዲወስዱ በምክረ ሃሳቡ አሳስቧል።

የድርጅቶቹን የሪፖርት ግኝቶች ተመርኩዘውም የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የአመፅ ድርጊቶቹን ያወገዙ ሲሆን፤ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ባወጣው መግለጫም "በእገታ ላይ የሚገኝ ማንኛውም ትግራዋይ እንዲለቀቅ" እና ዓለም አቀፍ ተመልካቾችም በሁሉም የእገታ ተቋማት ተገኝተው ምልከታ እንዲያደርጉ፤ እንዲሁም ጭካኔ የተመላባቸው የአመፅ ድርጊቶችን የፈፀሙ ማናቸውም ወገኖች ተጠያቂ እንዲሆኑና ተአማኒነት ያላቸው ምርመራዎችም እንዲካሔዱ ጥሪ አቅርቧል።
በሌላ በኩል ግና የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ኤፕሪል 10 ባወጣው መግለጫ "አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ሂውማንት ራይትስ ዎች በተደጋጋሚ ሪፖርቶቻቸው ሰብአዊነትን ሳይሆን ፖለቲካዊ ወገንተኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ይህ የፖለቲካ ወገንተኝነታቸው የሰብዓዊ መብት ጠለፋ (hijacking human rights) በሚል የሚያስተቻቸው ከመሆኑም በላይ በአንዲት ሉዓላዊት ሀገር የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀን ድርጅት (የህወሓትን) የፖለቲካ አቋም በሚጋራና የወልቃይት ጠገዴ የዐማራ ሕዝብን የዘመናት በደል በሚክድ ሁኔታ በሪፖርታቸው ወገንተኛ ሆነው መገኘታቸው የቆሙለትን ዓላማ እንደካዱ ይቆጠራል፡፡
"... በጥቅሉ በነዚህ እና የዐማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እየመረመራቸው በሚገኙ ሌሎች የሪፖርቱ አካል የሆኑና ለክልሉ ሕዝብ ሰላም መስፈንም ሆነ የሰብአዊ መብቶች መከበር የማይበጁ ስሁት ሀሳብና ብያኔዎች ምክንያት በሂዩማን ራይትስ ዎች እና በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የተዘጋጀውን የጋራ ሪፖርትን አንቀበለውም" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ - ፈረንሳይ
የመጀመሪያ ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫን በአምስት ፐርሰንት ቅድሚያ ማጠናቀቃቸው የተነገረላቸው ፕሬዚደንት ኢማኑኤል ማክሮን በሁለተኛነት ደረጃ ተከትለዋቸው ካሉት የቀኝ ክንፍ አክራሪ ብሔረተኛዋ ማሪን ለ ፔን ጋር ለዳግም የሁለተኛ ዙር ውድድር እየተሰናዱ ነው።

በአቶ ማክሮንና ወ/ሮ ለ ፔን መካከል የሁለተኛው ዙር ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የሚካሔደው ኤፕሪል 24 ይሆናል።

