የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የዓለም ጤና ድርጅት የአስትራዜኒካ ክትባት ዕድሚያቸው ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ ማናቸውም ሰዎች ለክትባትነት እንዲውል ድጋፍ መስጠቱን በመልካም ጎኑ መቀበላቸውን ገለጡ።
የዓለም ጤና ድርጅት ለክትባቱ ጥቅም ላይ መዋል ድጋፉን የሰጠው የተወሰኑ አገራት የአስትራዜኒካ ክትባት ፍቱንነት ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ይሁንታቸውን ለመቸር ውሳኔያቸውን ማዘግየታቸውን ተከትሎ ነው።
ቦሪስ ጆንሰን እስካሁን እንግሊዝ ውስጥ 90 ፐርሰንት ያህል ዕድሜያቸው ከ75 በላይ የሆኑትን አካትቶ ቁጥራቸው ከ30 ሚሊየን ያለፉ ሰዎች የኮሮናቫይረስ ክትባት መከተባቸውን አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የቪክቶሪያ ሆቴል ወሸባ ውስጥ የተከሰተው የቫይረስ ተዛማችነት ቁጥር እስከ ትናንት ስምንት የደረሰ ሲሆን፤ ዛሬ ከቀትር በኋላ ይፋ በሆነው ሪፖርት መሠረት ከሆሊዴይ ኢን ሆቴል ወሸባ ጋር ተያይዞ ሶስት ተጨማሪ ሰዎች በእንግሊዝ ቫሪየንት ቫይረስ የተጠቁ መሆናቸው ተገልጧል።
ይህም በጠቅላላው ቪክቶሪያ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሰዎችን ቁጥር ወደ 19 ከፍ አድርጎታል።
በትናንትናው ዕለት 22 ሺህ 570 የቪክቶሪያ ነዋሪዎች ምርመራ ያደረጉ መሆናቸውን አስመልክቶም የቪክቶሪያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ጃሲንታ "ይህ በከፍተኛ ቁጥር የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማድረግ የሚያመለክተውም ቪክቶሪያውያን ቫይረሱን በመከላከሉ ረገድ ያላቸውን ሚና በውል የተገነዘቡና ቫይረሱን ለመከላከልም ከፍ ያለ ትኩረት የሰጡ መሆናቸውን" የሚያመላክት መሆኑን በመግለጥ አድናቆታቸውን ገልጠዋል።
አክለውም የሆቴል ወሸባ ተላላፊ በሽታና ቁጥጥር ላይ የፕሮቶኮል ማሻሻያ እየተደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።
የሚያንማር ዕቀባ
ዩናይትድ ስቴትስ የአንግ ሳን ሱ ቺን በመፈንቅለ መንግሥት ከአመራር ማስወገድና ከሌሎች ገዲብ ፖለቲከኞች ጋር በወታደራዊው ቡድን ዘብጥያ መውረድ ጋር በተያያዘ በሚያንማር ላይ ወታደራዊ ዕቀባ ጥላለች።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደንና መንግሥታቸው በዩናይትድ ስቴትስ ለሚያንማር መንግሥት ተበጅቶ የነበረውን የድጎማ ገንዘብ የወታደራዊ ቡድኑ ጄኔራሎች እንዳያንቀሳቅሱት እንዲገታ ወስኗል።
ጆ ባይደን፤ "መፈንቅለ መንግሥቱን ባካሄዱት ወታደራዊ መሪዎች፣ የንግድ ጥቅሞቻቸውንና የቅርብ ቤተሰብ አባላቶቻቸው ማዕቀብ እንዲጣል ማዘዣ ፈርሜያለሁ። በዚህ ሳምንት ውስጥም የመጀመሪያ ዙር ዒላማዎች እንለያለን፣ በውጭ አቅርቦት ላይም ብርቱ ቁጥጥር እናደርጋለን። ለጤና ክብካቤ፣ ሲቪል ማኅበረሰብ ቡድናትና ሌሎች መስኮች ዘርፍ ለበርማውያን በቀጥታ ጥቅም ላይ የሚውሉትን ለይተን የምንደግፍ ሲሆን፤ የበርማን መንግሥት የሚደግፉ የዩናይትድ ስቴትስ ትሩፋቶችን ግና ተገተው እንዲቆዩ እናደርጋለን" ብለዋል።

