በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና የሕወሓት መሪ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል መካከል አሩሻ - ታንዛኒያ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ሊካሔድ ነው ተብሎ ስለሚነገርለት ድርድር በሁለቱም ወገኖች በኩል እስካሁን ይፋዊ መግለጫ አልተሰጠበትም።
የድርድሩን መካሔድ ከበርካታ የአፍሪካና ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ምንጮቼ አገኘሁ ብሎ ለአደባባይ ያበቃው የፈረንሳዩ ሌ ሞንድ ጋዜጣ ነው።
እንደ መረጃ ምንጮቹ አባባልም ከመጋረጃ በስተጀርባ በሚካሔደው ድርድር ላይ ከሁለቱም ተደራዳሪ ወገኖች በኩል አምስት-አምስት አባላት ያላቸው የልዑካን ቡድን እንደሚታደሙና የመነጋገሪያ አጀንዳዎቻቸውም ተኩስ አቁም፣ የሰብዓዊ ረድኤት አቅርቦት፣ እንደ መብራት፣ ባንክ፣ ነዳጅን የመሳሰሉ መሠረታዊ ግልጋሎቶች መቀጠል እንደሚሆኑና የወሰን ጉዳዮች ግና በአጀንዳነት ለንግግር እንደማይቀርብ ተጠቁሟል።
ይሁንና ሌ ሞንድ መቀመጫቸው አዲስ አበባ የሆነ አንድ ዲፕሎማትን በምንጭነት ጠቅሶ "የትግራይ አመራር የወልቃይን ጥያቄ በሂደት እንደሚተው" መግለጡን አስመልክቶ የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳን "እያንዳንዱን የትግራይ ስኩየር ኢንች ግዛት በሰላማዊም ሆነ በሌላ ማስመለስ የትግራይ መንግሥት ይፋ ዕሳቤና አቋም ነው። እናም በቅርቡ" አሰኝቷል።
ሆኖም አቶ ጌታቸው ድርድሩን አስመልክተው የማረጋገጫም ሆነ ማስተባባያ አስተያየት አልሰነዘሩም።
ትንናት ሰኔ 3 ሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸውን የሰጡት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲም በበኩላቸው፤ መንግሥታቸው ለሰላማዊ መፍትሔ ጥረት ቢያደርግም በሌላው በኩል ለጥቃት መዘጋጀት አሳሳቢ መሆኑን ከማመላከትና የዓለም አቀፉ ማኅበረስብም ድርጊቱን ይኮንን የሚል ጥሪ ከማቅረባቸው ባሻገር አሩሻ ላይ ለመካሔድ ታስቧል ስለተባለው ድርድር ይህ ነው ያሉት ነገር የለም።
በኢትዮጵያ መንግሥትና ሕወሓት መካከል ሰላማዊ መፍትሔ ለማፈላለግ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ኦባሳንጆ ጥረቶችን እያካሔዱ መሆኑ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ አማካይነት አሩሻ - ታንዛኒያ ከሚካሔድ ይልቅ ናይሮቢ ላይ በኬንያና አሜሪካ መራሽ አደርዳሪነት ቢካሔድ ውጤታማ ይሆናል ብለው አጀንዳ እየገፉ ያሉ ድምፆችም መሰማት ጀምረዋል።
ድልድይ
ሩስያና ቻይና ትናንት ዓርብ ሰኔ 3 ሁለቱን አገራት የሚያገናኝ አንድ ድልድይ አስመርቀው ከፍተዋል።
የድልድዩ ሥራ ላይ መዋልም የሁለቱን አገራት ንግድ እንደሚያጠናክር ብርቱ ተስፋ አሳድሯል።
ድልድዩ የሩስያ ከተማ የሆነችውን ብላጎቬሽቼንስክንና የቻይናዋን ሄሎንግጃንግ ከተማን የሚያገናኝ ነው።
ከአንድ ኪሎ ሜትር ጠቂት አለፍ ያለ ርዝመት ያለውን ድልድይ ለማሠራት 19 ቢሊየን ሩብል ወይም 486 ሚሊየን ዶላር ወጪን ፈጅቷል።
የድልድዩን ሥራ መጀመር አስመልክቶ የክሬምሊን የሩስያ ሩቅ ምሥራቅ ተወካይ ዩሪ ትሩትኔቭ "ተከፋፍሎ ባለ ዓለም ውስጥ የብላጎቬሽቼንስክ-ሄሎንግጃንግ በሩስያና ቻይና መካከል ልዩ ትርጓሜ አለው" ብለዋል።
በምርቃቱ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት የቻይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሁ ቹንሁዋ የድልድዩ ግብር ላይ መዋል የሁለቱን አገራት ትብብር ለጥልቅ ትስስር እንደሚያበቃ ተናግረዋል።
የሩስያ ትራንስፖርት ሚኒስትር ቪታሊ ሴቭሌይቭ በበኩላቸው ድልድዩ የሁለቱን አገራት የንግድ ልውውጥ ከአንድ ሚሊየን ቶንስ በላይ ከፍ እንደሚያደርግ ገልጠዋል።
ድልድዩ የተጀመረው በ2016 ሲሆን የተጠናቀቀው በ2020 ነው።
እስካሁን ተመርቆ ሥራውን እንዳይጀምር ሳንካ የሆነው የኮቪድ-19 ድንበር መሻገር ክልከላ ነበር።
በኤፕሪል ወር ሩስያ ከቻይና ጋር የሚኖራት የንግድ ልውውጥ በ2024 284 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ ገልጣለች።

