ዛሬ ፌብሪዋሪ 12 በቢጋ፣ ሞናሮ፣ ስትራትፊልድና ዎሉግቢ የተካሔደው የኒው ሳውዝ ዌይልስ 'ልዕለ ቅዳሜ' የሟሟያ ምርጫ ድምፅ መስጠት 6፡00 pm ላይ አብቅቷል።
- እንደ ABC የምርጫ ተንታኝ አንቶኒ ግሪን ትንበያ ለ33 ዓመታት በሊብራል ፓርቲ እጅ የነበረው ቢጋ ወደ ሌበር እጅ ሊገባ ይችላል።
- ሞናሮ ከናሽናልስ ፓርቲ እጅ ሳወጣ ፀንቶ ይቆያል
- ስትራትፊልድ የሌበርና ሊብራል ተቀራራቢ ድምፅ ያገኙ ቢሆንም ሌበር ከአጋር ፓርቲና የግል ተወዳዳሪዎች በሚያገኛቸው ተጨማሪ ድምፆች ታግዞ የስትራትፊልድን ወንበር ሊያገኝ ይችላል።
- የቀድሞዋ የኒው ሳውዝ ዌይልስ ፕሪሚየር የምክር ቤት ወንበር የነበረው ዎሉግቢ የተተኪያቸው የሊብራል ዕጩ ወንበር ሆኖ ይቀጥላል።
በኮቪድ-19 ሳቢያ ከ15 - 25 በፖስታ ድምፃቸውን የሰጡ በመሆኑ ጠቅላላ የድምፅ ውጤቱን ለማወቅ እስከሚቀጥለው ሳምንት መጠበቅን ግድ ይላል።
በአራቱም የሟሟያ ምርጫ በተካሒደባቸው የምርጫ ሥፍራዎች በርካታ ድምፆች ከሊብራልና ናሽናልስ ፓርቲዎች ወደ ሌበር አምርተዋል።
ዩክሬይን
የአውስትራሊያ መንግሥት ዩክሬይን በማንኛውም ያልታሰበ ወቅት በሩስያ ልትወረር ስለምትችል አውስትራሊያውያን በአስቸኳይ እንዲወጡ የጉዞ ማሳሰቢያ ሰጥታለች።
የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜሪዝ ፓይን የውጭ ጉዳይ ዲፓርትመንት ማሳሰቢያውን ዩክሬይን ላሉ አውስትራሊያውን ደጋግሞ ማቅረቡን ገልጠዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ዩናይትድ ስቴትስ ኪየቭ ያሉ የእኤምባሲ ሠራተኞችዋን ለማውጣት የወሰነች ሲሆን፤ ፕሬዚደንት ጆ ባይደንም ከሩስያው ፕሬዚደንት ፑቲን ጋር ነገ በስልክ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል።

