የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሚያዝያ 4 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን በፌዴራልና በክልል መደበኛ የጸጥታ ኃይሎች ውስጥ እንዲካተቱ በማድረግ መልሶ ለማደራጀት ያሳለፈውን ውሳኔና ትግበራ መጀመሩን ተከትሎ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ተቃውሞዎች፣ የጸጥታ መደፍረስ እና በአንዳንድ አካባቢዎች የደረሱ ግጭቶችንና ጉዳቶችን በተመለከተ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቋል።
በተለይም በቆቦ፣ በባሕር ዳር፣ በወረታ፣ በኮምቦልቻ፣ በደብረ ብርሃን እና በመራዊ የተቃውሞ ሰልፎች፣ መንገድ መዘጋት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እንዲሁም በጸጥታ ኃይሎች መካከል ፍጥጫዎች የተከሰቱ መሆኑን የገለጠው መግለጫ፤ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች በጸጥታ ኃይሎች በተወሰዱ እርምጃዎችና ለጊዜው ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች ሠራተኞችን ጨምሮ የሲቪል ሰዎች ሞት እና የአካል ጉዳት ማስከተሉን አመልክቷል።
በሌላ በኩል በእነዚህ ከተሞችና ሌሎችም አካባቢዎች በተፈጠረው ውጥረት፣ አለመረጋጋት፣ የአገልግሎት መቋረጥ እና የእንቅስቃሴ እገዳዎች ምክንያት በነዋሪዎች የዕለት ተዕለት ኑሮ እና ሥራ ላይ እንቅፋት ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡
ኢስመኮ "አጠቃላይ ችግሩና የጸጥታው ሁኔታ አስቸኳይ እልባት ካላገኘ ለከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ሥጋት በመሆኑ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በምክክርና በመግባባት እንዲፈቱ፣ በተለይም አጠቃላይ የፖለቲካ ነባራዊ ሁኔታው የፈጠረውን ሥጋትና የአለመተማመን ስሜት ከግምት በማስገባት መንግሥት የፖሊሲ ውሳኔውን አስፈላጊነትና ጠቀሜታ ለሚመለከታቸው ሁሉ በትዕግሥትና በጽሞና የሚያስረዳበትን ሁኔታ እንዲያመቻች፣ የጸጥታ አካላት ያልተመጣጠነ እና ሕይወት የሚያጠፋ ኃይል ከመጠቀም እንዲቆጠቡ፣ መንግሥት ስለደረሰው ጉዳት ሁሉ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ ተጠያቂነት እንዲያረጋግጥ እንዲሁም ሁሉም ሰው ሐሳቡን በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲገልጽ" ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቱ፤ ከመደበኛው የክትትል እና ምርመራ ሥራው ጎን ለጎን ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በሙሉ በማነጋገርና ምክረ ሐሳቦችን በመስጠት የተፈጠረው ችግር በውይይት እንዲፈታ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑንም ገልጧል።