ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ በዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ አብረዋቸው የሚታደሙ 10 አውስትራሊያውያንን መምረጣቸውን አስታወቁ።
አሥሩ አውስትራሊያውያን ለንግሥቲቱ የቀብር ሥነ ሥር ዓት ላይ የሚገኙት ባኪንግሃም ቤተመንግሥት ከርዕሰ መንግሥትና ርዕሰ ብሔሩ በተጨማሪ 10 የአውስትራሊያን ባሕልና ዕሴቶችን የሚያንፀባርቁ አውስትራሊያውያንም አብረው እንዲታደሙ በላከው ግብዣ መሠረት ነው።
በዚሁም መሠረት የ2022 የዓመቱ አውስትራሊያዊ ዲላን አልኮትንና የ2022 የኩዊንስላንድ የአካባቢ ጀግና ሽልማት ተሸላሚዋን ሳባ አብረሃምን አክሎ 10 የማኅበረሰብ አባላት አውስትራሊያውያንን ወክለው በቀብሩ ሥነ ሥርዓት ላይ ይታደማሉ።
አሥሩ አውስትራሊያውያን በዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ የቀብር ሥነ ሥ ርዓት ላይ ለመገኘት ወደ ለንደን የሚያቀኑት ከጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚና ጠቅላይ እንደራሴ ዲቪድ ሃርሌይ ጋር ነው። በለንደን የአውስትራሊያ ተጠባባቂ ከፍተኛ ኮሚሽነር ሊኔት ውድ ከመሪዎቹና የማኅበረሰብ አባላቱ ተወካዮች ጋር በጋራ ይታደማሉ።