ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም 'ምናልባትም ዓለም ለጥቁር ሕይወቶች የነጩን ያህል እኩል ትኩረት አይቸር ይሆናል' ሲሉ ሉላዊ ማኅበረሰቡ ላይ ነቀፌታ ሰነዘሩ

*** አውስትራሊያ የሰለሞን ደሴቶች ከቻይና ጋር የፀጥታ ስምምነት እንዳትፈራረም በይፋ ጠየቀች

News

World Health Organization (WHO) Director-General Tedros Adhanom Ghebreyesus. Source: Getty

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሉላዊው ማኅበረሰብ ለዩክሬይን ጦርነት የሰጠውን ትኩረት ያህል ሌሎች ሥፍራዎች ላይ ተከተው ላሉ ቀውሶች ተመሳሳይ ትኩረት አለመስጠቱን አመላክተው የሰላ ትችት ሰነዘሩ። 

ዋና ዳይሬክተሩ ነቀፌታቸውን የሰነዘሩት በአንድ በበይነ መረብ በተካሔደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል አሰቃቂ ሁነት ገጥሞት ሳለ በሚዲያ በኩል አግባብ ያለው ሽፋን እንዳልተሰጠው ተናግረዋል። 

ዶ/ር ቴድሮስ 'ምናልባትም ዓለም ለጥቁር ሕይወቶች የነጩን ያህል እኩል ትኩረት አይቸር ይሆናል' በማለትም ብርቱ ትችታቸውን አክለዋል።

አያይዘውም "እርግጥ ነው፤ ለዩክሬይን ሙሉ ትኩረት መስጠቱ በጣሙን ጠቃሚ ነው። ስለምን መላው ዓለም ላይ ተፅዕኖ አለውና። ይሁንና የዚያን ጥቂት ክፋይ ያህል እንኳ ለትግራይ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ሶርያና ለሌላው አልተቸረም። ያለማቅማማት ግልፅ መሆን እሻለሁ፤ ዓለም ሰብዓዊ ዝርያን እኩል አያስተናግድም። የተወሰኑት ከሌሎች የበለጠ ክብካቤ አላቸው" ብለዋል።  

አውስትራሊያና ሰለሞን ደሴቶች

 

የአውስትራሊያ ዓለም አቀፍ ልማትና የፓስፊክ ሚኒስትር ዜድ ሰሰልጃ ከሰለሞን ደሴቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው የሰለሞን ደሴቶችና የቻይና የፀጥታ ረቂቅ ስምምነት አውስትራሊያ ላይ ስጋት ያሳደረ መሆኑን ገለጡ። 

ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት በይፋ ሰለሞን ደሴቶች ከቤጂንግ ጋር በፀጥታ ስምምነት ላይ እንዳትፈራረም በአውስትራሊያ ስም ጥያቄ አቅርበዋል።

አቶ ሰሰልጃ ወደ ሰለሞን ደሴቶች መዲና ሆንያራ ያመሩት ማክሰኞ ዕለት ነው። 

ሚኒስትሩ ጉዟቸውን አስመልክተው ባወጡት መግለጫ "የሰለሞን ደሴቶችን ስምምነቱን እንዳትፈርምና ከፓስፊክ ቤተሰብ ጋር በቀጣናዊ ግልፅነት መንፈስ እንድትመክር በአክብሮት ጠይቀናል" ብለዋል።

News
Solomon Islands Prime Minister Manasseh Sogavare and Australia's Pacific Minister Zed Seselja met this week. Source: Supplied

ባለፈው ወር ሾልኮ በወጣው ረቂቅ የፀጥታ ስምምነት ቤጂንግ የባሕር ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት የፓስፊክ አገሯ ላይ ልታኖር ትችላለች የሚል ረቂቅ ዶክሜንት ተሰራጭቷል። 

ይሁንና የሰለሞን ደሴቶች ጠቅላይ ሚኒስትር ማናሴህ ሶጋቫሬ ቻይና ወታደራዊ ጦር ሠፈር ደሴቲቱ ላይ ልትከፍት ነው የሚለው "የሐሰት መረጃ" ነው ሲሉ አጣጥለውታል። 

አቶ ሰሰልጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ሶጋቫሬን "አውስትራሊያ የሰለሞን ደሴቶች የፀጥታ አጋር ምርጫ መሆኗንና ሰለሞን ደሴቶች በጭራሽ ለወታደራዊ ጦር ሠፈርነት መጠቀሚያ እንደማትውል" የሰጡትን ምላሽ በመልካም ማስተማመኛነት እንደሚቀበሉት ገልጠዋል። 

በሌላም በኩል በኢንዶ ፓስፊክ የዩናይትድ ስቴትስ የብሔራዊ ፀጥታ አስተባባሪ ከርት ካምፕቤል በቅርቡ የሰለሞን ደሴቶችን እንደሚጎበኙ ይጠበቃል። 

ባለፈው ወርሃ ፌብሪዋሪ ዩናይትድ ስቴትስ ሆንያራ ላይ ኤምባሲ እንደምትከፍት አስታውቃለች።

 

 

  

 


2 min read

Published

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now