አውስትራሊያ ዩናይትድ ስቴትስን ተከትላ ጦሯን ከአፍጋኒስታን ልታወጣ ነው

*** የአውስትራሊያ አየር መንገዶች በዚህ ዓመት መጨረሻ ዓለም አቀፍ በረራ ለማከናወን መሰናዷቸውን ጀምረዋል።

SBS Amharic

Source: SBS Amharic

ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን የአውስትራሊያ መከላከያ ኃይል የዩናይትድ ስቴትስን ጦር ተከትሎ በወርኃ ሴፕቴምበር አፍጋኒስታንን ለቅቆ እንደሚወጣ አስታወቁ። 

አፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኘው የአውስትራሊያ መከላከያ ጦር ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ1500 ተቀንሶ በአሁን ወቅት አፍጋኒስታን የሚገኙ ወታደሮች ቁጥር 80 ብቻ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አፍጋኒስታን ግዳጅ ላይ የተሰማሩና የተሰዉትን ወታደሮች አስመልክተ ሲናገሩ፤

"የአውስትራሊያን ወታደራዊ ግዳጅ ለመፈጸም አፍጋኒስታን የተሰዉ የአውስትራሊያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ለከፈሉት መስዋዕነት በክብር መዘከሩ ይቀጥላል። እንዲሁም፤ አፍጋኒስታን ወታደራዊ ግዳጃቸውን የተወጡትን እናመሰኛለን፤ በሕይወታቸው ላይም ያሳደረውን ተፅዕኖ እንገነዘባለን። ድጋፋችንን ለእነሱ ከመቸር ወደ ኋላ አንልም። ግጭቱ ብርቱ ተፅዕኖን በአፍጋኒስታን ሕዝብና ፕሬዚደንት ጋኒ ላይ አሳድሯል። ዳግም ከፊታቸው ተዘርግቶ ያለውን ውስብስብ ሰላምን የማስፈን ተግባር ለማገዝ ከጎናቸው እንቆማለን" ብለዋል።    

ለአውስትራሊያ ጦር አፍጋኒስታንን ልቅቆ መውጣት አስባቡ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን አፍጋኒስታን ውስጥ የሚገኙትን 2,500 ወታደሮች ከወርኅ ሜይ አንስቶ እስከ ሴፕቴምበር 11 አጠናቅቆ ለማስወጣት ከውሳኔ ላይ መድረስ ነው።

ውሳኔው የአሜሪካንን ረጅም ጦርነት ማክሰሚያ ይሆናል።  

ይህንኑ የባይደን ውሳኔ ተከትሎ የአፍጋኒስታን ፕሬዚደንት አሽራፍ ጋኒ በቲዊተር ገጻቸው ከአቶ ባይደን ጋር ሲነጋገሩ አገራቸው "እየተካሄዱ ያሉትን የሰላም ጥረቶች አስመልክቶ ከዩናይትድ ስቴትስና ኔቶ ሽርካዎቿ ጋር መሥራትዋን እንደምትቀጥል" የነገሯቸው መሆኑን አስታውቀዋል።  

የአውሮፕላን ጉዞ

የአውስትራሊያ አየር መንገዶች በዚህ ዓመት መጨረሻ ዓለም አቀፍ በረራ ለማከናወን መሰናዷቸውን ጀምረዋል።

 ቨርጂን አውስትራሊያ በ2021 መጨረሻ ሙሉ የበረራ አቅሙን ለመጠቀም ከበርካታ አውሮፕላኖቹና 220 የበረራ ሠራተኞቹ ጋር ወደ ሰማይ እንደሚመለሱ አስታውቋል። 

አየር መንገዱ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ፍላጎት ለማሟሟላት 10 ቦይንግ 737-800 አውሮፕላኖችን እንደሚያክል ገልጧል።

በሌላ በኩል የኳንታንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አለን ጆይስ የዓለም አቀፍ ጉዞና የድንበር ገደቦችን አስመልክቶ ከወዲሁ ፈጠን በማለት ውይይት ማካሄድ እንደሚያሻ አሳስበዋል።

ኳንታስ በኦክቶበር 31, 2021 ወደ 22 ዓለም አቀፍ የበረራ መዳረሻዎች ለመብረር ተልሟል።

 

የሥራ አጥነት ቁጥር

በጅሮንድ ጆሽ ፍራይደንበርግ የሥራ አጥነት ቁጥሩ መቀነስ የመንግሥት የምጣኔ ኅብት ማንሰራሪያ ዕቅድ የሚሠራ ስለመሆኑ የሚያመላክት እንደሆነ ተናግረዋል።

አውስትራሊያ ስታቲስቲክስ ቢሮ ዳታ መሠረት የሥራ አጥነት ቁጥር ወደ 5.6 የወረደ ሲሆን በወርኅ ማርች የሠራተኞች ቁጥር በ 70,700 ከፍ ብሏል።

የሙሉቀን ሠራተኞች ቁጥር በ20,800 ሲያሽቆለቁል፤ የግማሽ ቀን ሠራተኞች ቁጥር በ91,500 አሻቅቧል።

 ይሁንና የሥራጠባቂ ድጎማ በማክተሙ ሳቢያ ምን ያህል ተፅዕኖ በሥራ ፈላጊዎች ላይ እንዳሳደረ መረዳት የሚቻለው የፌዴራል በጀት በሜይ 20 ይፋ ከመደረጉ አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ በሚወጣው አውስትራሊያ ስታቲስቲክስ ቢሮ ዳታ ይሆናል።

ኮሮናቫይረስ

 

 የደቡብ አውስትራሊያ መንግሥት በወርኅ ጁን መጀመሪያ ግድም መጠነ ሰፊ የክትባት ማዕከላትን አቁሞ ክትባቶችን መስጠት እንደሚጀምር አስታወቀ።

ሶስት ሺህ የፋይዘር ክትባቶችን በሳምንት የሚሰጡ ጣቢያዎች እንደሚኖሩም ተገልጧል።

የቪክቶሪያ ተጠባባቂ ፕሪሚየር ጄምስ ሜርሊኖ በበኩላቸው መጠነ ሰፊ የክትባት መስጫ ጣቢያዎችን የማቆሙን እርምጃ እንደሚደግፉ ተናግረዋል።  

ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የኩዊንስላንድ መንግሥት ጥሎት የነበረውን የኮሮናቫይረስ ገደቦች ከዛሬ ሐሙስ ኤፕሪል 15 ጀምሮ በመላው ኩዊንስላንድ ያነሳ መሆኑን ይፋ አድርጓል።  

በዚህም መሠረት የፊት ጭምብልን የማጥለቅ ግዴታ ተነስቷል። የገበያ አዳራሾች፣ የቤት ውስጥ ግልጋሎት መስጫዎች፣ እንደ ሲኒማዎች፣ ቲያትሮችና ስታዲየሞችን የመሳሰሉቱ የመዝናኛ ሥፍራዎች  ወደ ቀድሞው 100 ፐርሰንት መስተንግዷቸው ይመለሳሉ።

እንዲሁም፤ የኩዊንስላንድ ነዋሪዎች በሆስፒታሎች፣ እሥር ቤቶች፣ የአረጋውያን መጠወሪያና በግብረ አካል ጉዳተኞች ማዕከላት ያሉ ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በአካል ተገኝተው መጎብኘት ይችላሉ። 

 

     

 

                                                         


3 min read

Published

By NACA

Presented by Kassahun Seboqa Negewo


Share this with family and friends


Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Watch now