የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለ ስልጣን የትግራይ ክፍለ አገር የበረራ መስመር ለአገር ውስጥና ለዓለም አቀፍ በረራዎች ክፍት መሆኑን አስታወቀ።
የበረራ መስመሩ ከሰኞ ታሕሳስ 5,2013 ከቀትር በኋላ እንደ ኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከ 8 ሰዓት ጀምሮ ግልጋሎት ጀምሯል።
ባለ ስልጣኑ አያይዞም በረራዎችን ማስተናገድ የሚችሉ የክፍለ አገሩ አውሮፕላን ማረፊያዎች ግልጋሎት መስጠት እንድሚችሉ ገልጧል።
በሌላም በኩል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለ ስልጣን ከእሑድ ታሕሳስ 4,2013 ጀምሮ የመቀሌ፣ ኩዊሃ፣ አዲጉዶምና የአካባቢ ከተሞች የመብራት ኃይል ግልጋሎት ማግኘት መጀመራችውን ገልጧል።
ባለ ስልጣኑ እንደጠቀሰውም ያሰማራቸው የጥገና ቡድን አባላት የጥገና ሥራዎቻቸውን በማከናወን በመተማ፣ ሁመራ፣ ወልቃይትና ማይጨው፣ አላማጣ፣ መኾኒ የመብራት ግልጋሎቶችን ማግኘት ጀምረዋል።
ኢትዮ ቴሌኮምም በድርሻው በመቀሌና በማይጨው የሞባይል ድምፅ ግልጋሎት መስጠት መጀመሩ ታሕሳስ 3,2013 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቀደም ሲልም በዳንሻ፣ በተርካን፣ በሁመራ፣ ሽራሮ፣ ማይጸብሪ፣ ማይካድራና በኮረም አካባቢዎች በከፊል በአላማጣ ሙሉ ለሙሉ ግልጋሎት በመስጠት ላይ እንዳለ ገልጧል።

