የቪክቶሪያ መንግሥት ሜልበርን ከተማና ሪጂናል ቪክቶሪያ ውስጥ በ$5.3 ቢሊየን 12,000 አዲስ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመሥራት ውጥን መንደፉን አስታወቀ።
ኖቬምበር 24 ይፋ በሚሆነው የ2020/21 ስቴት በጀት ውስጥ የታቀፈው ይኼ ዕቅድ 9,300 አዳዲስ ቤቶች የሚገነባና 1,100 አሁን ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን የሚተካ ይሆናል።
የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ እንዳሉት 2,000 አዲስ የሚገነቡት የጋራ መኖሪያ ቤቶች በአዕምሮ ሕመም ለተጠቁ፣ 2,900 በመጠነኛ ወጪ ተገንብተው ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰዎች መኖሪያ ይሆናሉ።
በተጨማሪም ከሚገነቡት ቤቶች ውስጥ 1,000 የሚሆኑት የቪክቶሪያ ነዋሪ ለሆኑ ነባር ዜጎች እንዲሁም ሌላ 1,000 ቤቶች የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ ለሆኑ መኖሪያ እንደሚሆኑ ፕሪሚየር አንድሩስ ተናግረዋል።
አያይዘውም፤ ፕሮግራሙ 10,000 ያህል ሥራዎች በየዓመቱ ለአራት ዓመታት እንደሚፈጥርና 6,000 መኖሪያ ቤቶችም በ18 ወራት ተሠርተው እንደሚጠናቀቁ ተናግረዋል።
የቤቶች ሚኒስትር ሪችድ ዌይን በበኩላቸው 25 ፐርሰንቱ የበጀቱ ድጎማ ለሪጂናል ቪክቶሪያ እንደሚውል ገልጠዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ
የቀኝ ፅንፈኞች ሚሊሺያዎችና ፕራውድ ቦይስ አብረው በተመሙበት የመዲናይቱ ዋሽንግተን በጠቅላይ ፍርድ ቤት ፊት ለፊት ሰልፍ ከሚወጡ የጸረ - ትራምፕ ሰልፈኞች ጋር ግጭት እንዳይቀሰቀስ ለመቆጣጠር ግዙፍ የሆነ የጸጥታ አስከባሪ ሃይልም ተገኝቷል።
ለትራምፕ ደጋፊዎች ሰልፍ መውጣት አስባብ የሆነው ዶናልድ ትራምፕ 'የምርጫ ማጭበርበር ተፈጽሞ ድሌን ተነጥቄያለሁ' ሲሉ ማስረጃ አልባ እሮሮ ማሰማታቸውን ተከትሎ ነው።
አቶ ትራምፕም ድጋፋቸውን ለማሳየት ሰልፈኞቹ በተገኙበት አደባባይ በሞተረኛ በታጀበ አውቶሞቢላቸው አቋርጠዋል።
በወቅቱም ሰልፈኞቹ የድጋፍ ጩኸትና ፉጨት አሰምተዋል። ባንዲራዎቻቸውንም አውለብልበዋል። "ታይቶ የማይታወቅ ምርጥ ፕሬዚደንት"፣ "ስርቆት ይቁም"፣ "አራት ተጨማሪ ዓመት" ሲሉም ድምጻቸውን አስተጋብተዋል።

እስካሁን ይፋ በሆኑት የምርጫ ውጤቶች የትራምፕ ተቀናቃኝ የነበሩት የዲሞክራቱ ጆ ባይደን 306 የምርጫ ኮሌጅ ድምፆችን ሲያገኙ አቶ ትራምፕ 232 አግኝተዋል።
አንድን ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ለፕሬዚደንትነት የሚያበቁት 270 የምርጫ ኮሌጅ ድምፆች ናቸው።

