አውስትራሊያውያን ለነባር ዜጎች ቀዳሚ ባለ አገርነትና ድምፅ ለፓርላማ ቋሚ አማካሪ አካልን ለማቆም በድጋፍና ተቃውሞ በሰጡት ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ ተቃውመዋል።
በድምፅ አሰጣጡ ከአውስትራሊያ መዲና ግዛት በስተቀር በተቀሩት ከፍለ አገራትና ሰሜናዊ ግዛት የይሁንታ ድምፃቸውን ነፍገዋል።
ውጤቱን ተከትሎ ትናንት ማምሻውን ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ለመላ አውስትራሊያውያን ባደረጉት ንግግር የሕዝበ ውሳኔውን ብይን እንደሚያከብሩ ገልጠው ፤ ሆኖም የነባር ዜጎችን ሕይወት ለማቃናት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የፌዴራል መንግሥቱ ነባር ዜጎች ሚኒስትር ሊንዳ በርኒ ከጠቅላይ ሚኒስትር አልባኒዚ ቀጥለው ለነባር ዜጎች በቀጥታ ባስተላልፉት መልዕክት፤
"ያለፉት ጥቂት ወራት አዋኪ እንደነበሩ አውቃለሁ፤ ሆኖም በማንነታችሁ ኩሩ፣ በ65 ሺህ ዓመታት ታሪካችሁ፣ ባሕላችሁና እዚህች አገር ውስጥ ባላችሁ ተገቢ ሥፍራ ኩሩ። ወደ ፊት በመራመዱና በመመንደጉ እንቀጥላለን" ሲሉ የማፅናኛና ማበረታቻ ቃሎቻቸውን ቸረዋል።
በሌላ በኩል የሕዝበ ውሳኔው አይሁን ጎራና የፌደራል ተቃዋሚ ቅንጅት ቡድን መሪ ፒተር ዳተን በበኩላቸው፤
"በቅንጅቱ በኩል እንደማናቸውም አውስትራሊያውያን ሁሉ የነባር ዜጎች እክሎች መፍትሔ እንዲያገኙ እንሻለን። እኛ የምንቃወመው የይሁንና አይሁን ድምፅ ሰጪዎች የድምፅ ለፓርላማ መፍትሔ መሆንንና አለመሆንን ነው። እኒህ የአተያይ ልዩነቶች አንዳችን ለአንዳችን ያለንን ወይም ለአገራችን ያለንን ፍቅር አይከላውም" ብለዋል።

የተቃዋሚ ቡድኑ የነባር ዜጎች ቃል አቀባይዋ ሴናተር ጃሲንታ ፕራይስ በፊናቸው "አውስትራሊያውያን ሕገ መንግሥታችን የዘር መስመርን ለተከተለ ልዩነት አይሁን ብለዋል" ሲሉ ውጤቱን በመልካም ጎኑ የተቀበሉት መሆኑን ገልጠዋል።
መካከለኛው ምሥራቅ
በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን የእሥራኤል ጦር የምድር ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት ቀዬዎቻቸውን ለቅቀው መውጣት ጀምረዋል።
እሥራኤል የአየርና የባሕር ጥቃት እያካሔደች ሲሆን፤ የእሥራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሪር አድሚራል ዳንኤል ሃጋሪ በቅርቡ ጋዛ ላይ የምድር ጦራቸው ጥቃት እንደሚሰነዝር አስታውቀዋል።
ኦክቶበር 7 / መስከረም 26 ሃማስ እሥራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረ አንስቶ 3,200 ያህል ሰዎች በፍልስጤምና እሥራኤል በኩል ሕይወታቸውን አጥተዋል።

