ቪክቶሪያ ውስጥ ባለፉት 24 ሰዓታት በኮሮናቫይረስ 42 ሰዎች ቢጠቁም የአንድም ሰው ሕይወት ለሕልፈት አልተዳረገም።
አንድ ሞት ካልተመዘገበባት ጁላይ 13 ወዲህ ቪክቶሪያ ውስጥ አንድ የሰው ሕይወት በቫይረሱ ሳቢያ ሳያልፍ ሲቀር ይህ የመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ይህንንም ተከትሎ በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ የሪጂናል ቪክቶሪያ የኮቪድ - 19 ገደቦች ከደረጃ 4 ወደ ደረጃ 3 ይሸጋገራል።
የሪጂናል ቪክቶሪያ የ14 ቀናት የቫይረሱ ተዛማችነት አማካይ ቁጥር 3.6 ሲሆን የሜልበር 52.9 ደርሷል።
ሜልበርን ላይ ተጥለው ያለሉትን የደረጃ 4 ገደቦች ለማላላት የተቀመጠው መመዘኛ ከሴፕቴምበር 28 በፊት አማካይ የ14 ቀናት ተዛማች የቫይረስ መጠን ከ30 እስከ 50 መድረስ ነው።
ኦነግ
"የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የታገዱት ፓርቲውን ለመታደግ ሲባል" መሆኑን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ አስታውቋል።
አቶ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው ለማገድ ግድ ያሰኘው "አቶ ዳውድ በፓርቲው አንድነትና ሰላማዊ ትግል ላይ እየፈጠሩት የነበረውን ችግር ለመቅረፍ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢደረጉም ያሉባቸውን ችግሮች ከማስተካከል ይልቅ ፓርቲውን የመከፋፈልና አንጃ የመፍጠር አካሄዶችን ሲከተሉ ቆይተዋል። በመሆኑም ለፓርቲው ህልውናና ጥንካሬ ሲባል የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቶ ዳውድ ኢብሳን ከፓርቲው አግዷቸዋል" በማለት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለኢፕኤ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

አክለውም "ቀደም ባሉት አመታት ሶስት ጊዜ ለፓርቲው መከፋፈል ዋናው ምክንያት እርሳቸው እንደነበሩና አሁንም ለአራተኛ ጊዜ ፓርቲውን ለመከፋፈል አንጃ ፈጥረው ሲንቀሳቀሱ ቆይተዋል። ይህንን ለማስተካከል ጥረት ሲደረግም በተጨባጭ የፓርቲውን ንብረትና ገንዘብ ወደግላቸው የማዘዋወር እንቅስቃሴ ውስጥ ገብተዋል። ስለሆነም ፓርቲውን ለመታደግ ሲባል የእገዳ እርምጃው ተወስዶባቸዋል" በማለት ተናግረዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጠቅላላ ጉባዔ ተደርጎ አዲስ መሪ ኣስኪመረጥ ድረስ የድርጅቱ ተወካይና መሪ ሆነው የሚሰሩት ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ መሆናቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።

