ባለፉት 24 ሰዓታት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መስፋፋት አሽቆልቁሎ በዛሬው ዕለት እሑድ ቪክቶሪያ ውስጥ 278 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል፤ 16 ሕይወታቸው አልፏል።
ባለፉት ሁለት ቀናት 303 ቅዳሜ እንዲሁም 372 በዕለተ ዓርብ ቪክቶሪያውያን በኮቪድ - 19 ተይዘዋል።
በዛሬው ዕለት ሕይወታቸው ካለፉት ውስጥ አንዲት ሴትና ሁለት ወንዶች በ70ዎቹ፣ ሁለት ሴቶችና አራት ወንዶች በ80ዎቹ፣ አራት ሴቶችና ሶስት ወንዶች በ90ዎቹ ዕድሜ ያሉ እንደነበሩ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ አስታውቀዋል።
ከሟቾቹ ውስጥ አሥራ አንዱ የአረጋውያን መጦሪያ ቤቶች ተጠዋሪዎች ናቸው።
እስካሁን ቪክቶሪያ ውስጥ በጠቅላላው 16,764 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተው ያሉ ሲሆን 660 ሆስፒታል ተኝተው ሕክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ።
በፅኑ ሕመምተኛ ክፍሎች 40 ሕሙማን ሲገኙ 29ኙ በሰው ሠራሽ መተንፈሻ መሳሪያዎች እየተረዱ ነው።
አፋር - እርዳታ
የአማራ ክልላዊ መንግሥትና የገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአፋር ክልል በጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች እርዳታዎቻቸውን አበርክተዋል።
የአማራ ክልላዊ መንግሥትና የገቢዎች ሚኒስቴር ከለገሷቸው ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የምግብና አልባሳት እርዳታዎች ውስጥ 500 ብርድ ልብሶች፣ 500 ጥንድ አንሶላዎች፣ 500 ፍራሽና 1 ሺህ 500 ኩንታል የምግብ እህል ይገኙበታል።
ሠመራ ከተማ በመገኘት ዛሬ ድጋፉን ያደረጉትና ሌሎችም አካላት በጎርፍ የተጎዱ አካባቢዎችንም ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
ችሮታቸውን ሰመራ ከተማ በመገኘት በክፍለ አገራቸው ስም ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ያበረከቱት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር "ሁላችንም የሉሲ ልጆች በመሆናችን የአፋር ሕዝብን መደገፍ የራሳችንን ሕዝብ እንደመደገፍ ነው" ብለዋል።
ድጋፉም በጎርፍ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እስኪመለሱ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
በርዕሰ መስተዳድሩ በኩል የቀረበው ድጋፍ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሲሆን በአማራ ክልል ገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በክልሉ ከ46 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ልዩ ልዩ አልባሳት፣ ስኳር፣ የምግብ ዘይት፣ ሩዝ፣ የዱቄትና ፓስታ እገዛ ተበርክቷል።
የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባም በበኩላቸው በጎርፍ አደጋ ለተጎዱት “ይህም ሁላችንም በአንድ ላይ ስንቆም ችግሮችን በራሳችን አቅም መፍታት እንደምንችል ማሣያ ነው፤ ወንድማማችነትንና አንድነቱን የሚጠናክር ነው” በማለት በክልሉ ሕዝብና መንግሥት ስም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለጎርፍ ጉዳተኞቹ የሚውል ሶስት ሚሊዮን ብር የሚገመት የምግብና መድኃኒት እርዳታ ቸሯል።
እርዳታውን ለአፋር ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ልማት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ያስረከቡት የኦሮሚያ ክልል ልዑካን ቡድን አባል አቶ ንብረቱ ታረቀኝ ሲሆኑ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ቃል ገብተዋል።
የአፋር ክልል አደጋ መከላከል ምግብ ዋስት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴንም በበኩላቸው "የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ያደረገው ድጋፍ የኢትዮጵያውያንን የመረዳዳት ባሕል በተግባር ያሳየ ነው፤ የደረሰው የጎርፍ አደጋ በኅብረተሰቡና በክልሉ አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ተመሣሣይ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ" ለኢትዮጵያውያን ወገኖች ሁሉ ጥሪ አድርገዋል።
አያይዘውም፤ በአፋር ክልል በቅርቡ ተከስቶ በነበረው የጎርፍ አደጋ ከ40 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጠዋል።

