ከታህሳስ 4 እስከ 6 ተካሒዶ የተጠናቀቀው የዩናይትድ ስቴትስና አፍሪካ አገራት መሪዎች ጉባኤ ላይ 49 የአፍሪካ አገራት መሪዎች ተጋብዘዋል። ጉባኤው መሠረቱን ያደረገውም በጋራ መከባበር፣ የጋርዮሽ ጥቅሞችና ዕሴቶችን መርህ እንደነበር ተመልክቷል።
ጉባኤውን በንግግር የዘጉት የአስተናጋጇ አገር ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን "የአፍሪካውያን ድምፆች፣የአፍሪካውያን አመራር፣ የአፍሪካውያን ፈጠራ" አንገብጋቢ ሉላዊ ችግሮችን በመክላት የጋራ ርዕዮቻችን የሆኑትን ነፃ፣ ግልፅ፣ የበለፀገችና ደህንነቷ የተጠበቀ ዓለም ዕውን ለማድረግ ወሳኝ እንደሆኑ አመላክተዋል።
አፍሪካ በእያንዳንዱ ሉላዊ ተግዳሮቶች ላይ ውይይቶች በሚካሔድበት ክፍል ጠረጴዛ ዙሪያና ተቋማት ውስጥ ውክልና ሊኖራት እንደሚገባ እንደሚያምኑ በመግለጽ፤ በመስከረሙ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ወቅትም ዩናይትድ ስቴትስ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ክለሳን ሙሉ ለሙሉ እንደምትደግፍና አፍሪካም ቋሚ ውክልና እንዲኖራት አቋማቸውን ያንፀባረቁ መሆኑን አውስተዋል።
ያንንም ተከትሎ፤ በዕለቱ የአፍሪካ ኅብረት በቡድን 20 ቋሚ አባልነት እንዲኖረው ጥሪ አቅርበዋል።
አክለውም፤ ከዩናይትድ ስቴት ስ ኮንግረስ ጋር በቅርብ ትብብር በመሥራት 55 ቢሊየን ዶላርስ በመመደብ የአፍሪካን 2063 ቀዳሚ አጀንዳ ወደፊት ለማራማድ እንዲያስችል መወጠኑን ጠቁመዋል። ይህም ለአፍሪካ ሕዝብ፣ ለአፍሪካ መሠረተ ልማት፣ ለአፍሪካ ግብርና፣ ለአፍሪካ ጤና ሥርዓትና ለሌሎችም ተግባራት የሚውል መሆኑን ፕሬዚደንቱ አመላክተዋል።
እንዲሁም፤ኮንግረስ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላላቸው አገራት መደጎሚያነት የሚውል 21 ቢሊየን ዶላርስ ለዓለም አቀፉ ገንዘብ ድርጅት ለማበደር ይሁንታውን እንዲቸር መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ የድምፅ ምዝገባ፣ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሽያ ላይ በማዋል ዲሞክራሲን ለማጎልበት እንዲያስችል 75 ሚሊየን ዶላርስ ለመንግሥታዊ ግልፅነትና ተጠያቂነትነት ማጠናከሪያ ላይ እንዲውል አስተዳደራቸው በቅርበት ከኮንግረስ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራ፤ በተጨማሪም ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር በሽርካነት የአፍሪካን የፀጥታ ብቃት ከፍ ለማድረግ የ100 ሚሊየን ዶላር አስኳል ፕሮግራም የሚዘረጋ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በሌላም በኩል፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ እንዳስታወቀው የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የጤና አገልግሎቶችና የጎርፍ ፕሮጄክቶች ሥራ ማስፈፀሚያ የሚሆን 745 ሚሊየን ዶላር መፍቀዱን ገልጧል።
ፕሬዚደንት ባይደን ለአፍሪካውያኑ መሪዎችና ቀዳማዊት እመቤቶች በዋይት ሐውስ የእራት ግብዣ በማድረግ አስተናግደዋል።

