የፈዋሽ ቁሶች አስተዳደር (TGA) በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ለኮሮናቫይረስ መከላከያ የተሠራው ክትባት አውስትራሊያ ውስጥ ለክትባትነት እንዲውል ይሁንታ ሰጠ።
አስተዳደሩ ባለፈው ወር ለፋይዘር ክትባት አውስትራሊያ ውስጥ ጥቅም ላይ መዋል ይሁንታውን ቸሯል።
አብዛኛውን ለክትባትነት ጥቅም ላይ እንዲውል የታሰበው የአስትራዜኒካ ክትባት ሲሆን ሜልበርን ውስጥ በወር አንድ ሚሊየን ለማምረት ዕቅድ ተይዞለታል።
የአስትራዜኒካ ክትባት በአስተዳደሩ ይሁንታ ያገኘው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ ነው።
ምንም እንኳ ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ የጥንቃቄ ስጋት የማይፈጥር ቢሆንም በእዚህ ዕድሜ ምድብ ላሉ ሰዎች ክትባቱ የመስጠቱ ውሳኔ እንደተከታቢው ግለሰብ ሁኔታ ይወሰናል። በሌላም በኩል በእዚህ ዕድሜ ክልል ላሉ ሰዎች ቫይረሱን የመከላከል ፍቱንነቱን አስመልክቶ እስካሁን አጥጋቢ የሆነ ዳታ አልተሰባሰበም።
አውስትራሊያ 53.8 ሚሊየን አስትራዘኒካ ክትባቶችን አግኝታለች።
ምርጫ ኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በትናንትናው ዕለት ለዘንድሮው የኝቦት 2013 አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪዎች የመልካም ምኞትና የማሳሰቢያ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የቦርድ ሰብሳቢዋ የፓርቲ አመራር አባላት፣ የፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎችና የግል ዕጩ ተወዳዳሪዎች የምርጫውን ሂደት "በዝለት ሳይሆን በጥንካሬ" እንዲጀምሩ አበረታተዋል።
አያይዘውም "ዛሬ ለ6ኛው አጠቃላይ ምርጫ በእጩነት ስትመዘገቡ ወይም እንደ ፓርቲ እጩዎቻችሁን ስታስመዘግቡ ከፊታችን ያለው መንገድ ከፊል ተስፋ ከፊል ስጋትን አዝሎ እንደሚጠብቃችሁ እንደሚጠብቀን ለሁሉም ግልፅ ነገር ይመስለኛል፡" ብለዋል።
ቦርዱ ምርጫው በስኬት እንዲከናወን ስለ ስንዱነቱ፣ የዳበረ አቅም ስለማፍራቱና ገለልተኝነቱ ሲገልጡም "በቀደሙ ምርጫዎቻችን ባልነበረ ሁኔታ የሂደቱን ዋና ተዋናዮች ማለትም ተፎካካሪዎቹን ግራ ወይም ቀኝ፣ ትንሽ ወይም ትልቅ፣ አገራዊ ወይስ ክልላዊ ሳይል፣ በጥረታቸው ሊያግዝ እና ሳንካቸውን ሊፈታ የተዘጋጀ፣ አቅሙን የጨመረ፣ የገለልተኝነቱን መጠን እና ስፋት ከተፅእኖ ሁሉ የሚከላከል የምርጫ ቦርድ ሂደቱን እያስተዳደረ ይገኛል" በማለት አስረድተዋል።
መልዕክታቸውንም ለተወዳዳሪዎቹ መልካም የምርጫ ዘመን እንዲሆንላቸው በመመኘት ቋጭተዋል።

