የጋዛን ጦርነት ለመግታት፣ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ታጋቾችንና እሥረኞችን ለማስለቀቅ የሚያስችል የተኩስ አቁም ስምምነት በእሥራኤልና ሃማስ መካከል መደረሱን የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼህ መሐመድ ቢን አብዱልራህማን አል ትሃኒ አስታወቁ።
አክለውም፤ የተኩስ አቁሙ የሚተገበረው ከእሑድ ጃኑዋሪ 19 / ጥር 11 ጀምሮ እንደሆነና ትክክለኛው ሰዓትም በቅርቡ ይፋ እንደሚሆን፤ እንዲሁም የስምምነቱ ምዕራፍ አንድ ሂደት ለ42 ቀናት እንደሚቀጥል አክለው ገልጠዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን በበኩላቸው የተኩስ አቁሙን ስምምነት በመልካም ጎኑ መቀበላቸውን አስታውቀዋል፤ ከኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ጋርም ስምምነቱ ይፋ መሆኑ ከተገለጠ ጥቂት ደቂቃዎች በኋላ በስልክ ተነጋግረዋል።
አቶ ባይደን፤ እሥራኤልና ሃማስ ከስምምነት ላይ የደረሱት እሳቸው በወርኅ ሜይ 2023 ያቀረቡትን ረቂቅ የስምምነት ማዕቀፍ ተከትሎ መሆኑን አመላክተዋል።
በማያያዝም ፤ ተኩስ አቁሙ ሶስት ምዕራፎች እንዳለውና ይህም የእሥራኤልን ከጋዛ ቀዬዎች ለቅቆ መውጣትንና የታጋቾችን መለቀቅ እንደሚያካትት ጠቅሰዋል።
በአውስትራሊያ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነቱን በማለፊያነት እንደሚቀበሉትና ሁለቱም ተስማሚዎች ለዘላቂ ሰላም ሰፈና ስምምነቱን እንዲያከብሩ አሳስበዋል።
የታጋቾች ቤተሰቦችና ወዳጆች ስምምነቱን አስመልክቶ ደስታቸውን ቴሌአቪቭ ላይ ገልጠዋል።

የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ የጋዛ ነዋሪዎችም የተሰማቸውን እፎይታ ጎዳናዎች ላይ በመውጣት አንፀባርቀዋል።
እሥራኤል የሃማስን ኦክቶበር 7 ጥቃት ተከትሎ 30 ሕፃናትን አክሎ የ1,200 ሰዎቿን መገደልንና ከ200 በላይ መታገት ሳቢያ ከ15 ወራት በላይ የዘለቀ ወታደራዊ የአፀፋ እርምጃ ወስዳለች።

በሳቢያውም፤ በጋዛ ጤና ሚኒስቴር ሪፖርት መሠረት ከኦክቶበር 7 አንስቶ 14 ሺህ ሕፃናት ጨምሮ ከ46,000 የጋዛ ነዋሪ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል።

