ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ይቋረጣል ተብሎ የታሰበው የወረርሽኝ የሥራ ፈቃድ ክፍያ እንደሚቀጥል አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠራተኛ ማኅበራትና የረድኤት ድርጅቶችን ጥሪ ተከትሎ የፌዴራል መንግሥቱ የ $750 የወረርሽኝ የሕክምና ፈቃድ ክፍያ መቀጠልን ያስታወቁት ዛሬ ከቀትር በኋላ በጠሩት ጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት ነው።
ቀደም ሲል የፌዴራል መንግሥቱ ከቀድሞው መንግሥት የተጫነበት ከአንድ ትሪሊየን ዶላር በላይ ዕዳ ያለበት በመሆኑ በክፍያው ለመቀጠል እንደሚያውከው አመላክቶ ነበር።
ሆኖም የኩዊንስላንድ መንግሥት በጠራው አስቸኳይ የብሔራዊ ካቢኔ ስብሰባ ላይ የተመከረበት በኮቪድ-19 የተጠቁ ሠራተኞች ከሥራ ገበታ በሚቀሩበት ወቅት ክፍያ እንዲያገኙ ለማስቻል የፌዴራልና የክፍለ አገራት መንግሥታት የወጪውን እኩሌታ በመጋራት ለመሸፈን ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የአስቸኳይ ጊዜ የድጋፍ ክፍያው የሚዘልቀው እስከ ወርሃ ሴፕቴምበር መጨረሻ ይሆናል።
የጠፈር ጉዞ
ሩስያና ዩናይትድ ስቴትስ በዩክሬይን ጦርነት ሳቢያ በመካከላቸው የተፈጠረውን ጆኦፖለቲካዊ ውጥረት ወደ ጎን ብለው ከዓለም አቀፍ የጠፈር ጣቢያ በጋራ ለመምጠቅ ከስምምነት ላይ ደረሱ።
በስምምነቱም መሠረት የዩናይትድ ስቴትስ ጠፈርተኞች ወደ ሩስያ ተጉዘው በሩስያ ሶዩዝ የሕዋ መንኮራኩር የሚጓዙ ሲሆን፤ የሩስያ ጠፈርተኞችም ወደ ዩናይትድ ስቴትስ አምርተው ከፍሎሪዳ በምትመጥቀው ሕዋ ኤክስ ሮኬት ተጓዥ ይሆናሉ።