ከኖቬምበር 15 - 2020 ጀምሮ ከአንድ አሠርት ዓመት በኋላ "የአውስትራሊያ ዕሴቶች" ላይ ያተኮረ የዜግነት ፈተና አሰጣጥ ለውጥ ይደረጋል።
በለውጡ ላይ ሌሎች ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መሥፈርቶች ላይ የተደረገ ማሻሻያ የሌለ ሲሆን በፈተናው ላይ የሚቀርቡ አምስት "የአውስትራሊያ ዕሴቶች" ጥያቄዎችን በትክክል መመለስ ግና ግዴታ ነው።
ተጠባባቂ የኢሚግሬሽን፣ ዜግነት፣ የመጤ ግልጋሎቶችና መድብለባሕል ጉዳዮች ሚኒስትር አላን ታዥ " የኛ የአውስትራሊያ ዕሴቶች ጠቃሚ ናቸው። አገራችንን ለመቅረፅ ረድተዋል። ለዚያም ነው አያሌ ሰዎች የአውስትራሊያ ዜጎች ለመሆን የሚሹት"
"የተሻሻለው የዜግነት ፈተና ዜጋ መሆን ለሚሹ አዲስና ይበልጡን ትርጉም ያላቸው ጥያቄዎች ይኖሩናል፤ ዕሴቶቻችን ስለሆኑት የንግግር ነፃነት፣ የጋራ መከባበር፣ የመልካም ዕድሎች ዕኩልነት፣ የዲሞክራሲና የሕግ የበላይነት ጠቀሜታዎች ግንዛቤና እንዲኖራቸውና ለማክበርም ቃል እንዲገቡ"
"ለዜግነት የሚያመለከቱ ለአገራችን የላቀ ቃል ከመግባታቸው በፊት ዕሴቶቻችንን በውል እንዲረዱልንም እንጠይቃለን" ብለዋል።
ከኦክቶበር 30 ጀምሮ የቪዛና ዜግነት አመልካቾች አዲስ የተሻሻለውን የአውስትራሊያ ዕሴቶች በውል መገንዘብና መቀበል ይጠበቅባቸዋል።
የዜግነት ፈተናው 20 የምርጫ ጥያቄዎችን የያዘ ሲሆን አምስቱን የአውስትራሊያ ዕሴቶች ጨምሮ ለማለፍ ቢያንስ 75 ፐርሰንት ውጤት ማምጣት ግድ ይላል።
አዲሱን የተሻሻለ የአውስትራሊያ ዕሴቶች ለመረዳት An updated version of the Australian Citizenship: Our Common Bond በሚል የተዘጋጀውን ዳውሎድ ማድረግ ይቻላል።
በዛሬዋ የዜግነት ቀን ከ2500 በላይ ነዋሪዎች የአውስትራሊያን ዜግነት ከ 100 በላይ በሆኑ የዜግነት ሥነ ሥርዓት ሥፍራዎች ተቀብለዋል።
ባለፈው ዓመት 204,000 ሰዎች የአውስትራሊያ ዜጋ ሆነዋል።
ኮቨድ-19 ተንሰራፍቶ ባለበት ወቅት ከማርች 31 - 2020 ጀምሮ ከ85,000 በላይ ሰዎች በኦንላይን በተካሄዱ ሥነ ሥርዓቶች የአውስትራሊያ ዜግነትን ወስደዋል።
ከቪክቶሪያ በስተቀር የዜግነት ፈተና በመላው አውስትራሊያ ይቀጥላል።
ኮሮናቫይረስ - ቪክቶሪያ
በዛሬው ዕለት ቪክቶሪያ ውስጥ 28 ሰዎች በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሲሆን ስምንት ሕይወታቸውን አጥተዋል።
በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ዕለታዊ ቁጥር ከ30 በታች የተመዘገበው ጁን 24 ሲሆን ቁጥሩም 29 ነበር።
የሜልበርን አማካይ የ14 ቀናት የቫይረስ ቁጥር 44.4 ሲደርስ የሪጅናል ቪክቶሪያ 2.9 ፐርሰንት ደርሷል።
በቪክቶሪያ የኮቨድ-19 ማንሰራሪያ ፍኖተ ካርታ መሠረት ተጥለው ያሉ ገደቦችን በሴፕቴምበር መገባደጃ ላይ ለማላላት የ14 ቀን አማካይ የቫይረስ ቁጥር ከ30 እስከ 50 እንዲደርስ ይጠበቃል።
በጥቅሉ ቪክቶሪያ ውስጥ 745 ሰዎች በቫይረሱ ሳቢያ ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።

