የአውስትራሊያ ሥራ አጥነት ቁጥር ባለፉት ወራት በዝቅተኛነቱ አዲስ ሬኮርድ አስመዝግቧል። ይሁንና ትሩፋቶቹ ለሁሉም የተዳረሰ አይደለም።
የዋጋ ግሽበት ንሮ ያለ ቢሆንም ዛሬ ሐሙስ በአውስትራሊያ ስታቲስቲክስ ቢሮ ይፋ በተደረገው መሠረት የአውስትራሊያ ሥራ አጥነት ቁጥር ከ3.5 ፐርሰንት ወደ 3.4 ወርዷል። ይህም ከ1974 ወዲህ በዝቅተኛነቱ የመጀመሪያው ሆኗል።
በጁን / ሐምሌ የአውስትራሊያ ስታቲስቲክስ ቢሮ ዳታ እንዳመለከተው ከሆነ 23.5 ፐርሰንት ሥራ አጥነት ተከስቶ ያለው እንግሊዝኛ ቋንቋ አፍ መፍቻቸው ያልሆነ ማኅበረሰባት ዘንድ ነው።
የእንግሊዝኛ ቋንቋ እጥረት፣ የዳበረ የአውስትራሊያ ሥራ ልምድ አለመኖር፣ ውስን ማኅበራዊ አውታረ መረብ፣ የአገር ቤት ክህሎትና የሙያ ብቃት ተቀባይነት አለማግኘት እንግሊዝኛ ተናጋሪ ላልሆኑ ሥራ ፈላጊዎች አንኳር ተግዳሮቶች ሆነው ተገኝተዋል።