የአውስትራሊያ ፓርላማ በዛሬው ዕለት በሚታደምበት ወቅት የፌዴራል ሌበር ምክር ቤት አባል አንቶኒ ባይረንን የሰሉ የስልክ የጽሑፍ ትችት መልዕክቶችን በተመለከተ ሌበር ብርቱ መጠይቆች ይጠብቁታል።
የቪክቶሪያ ሌበር ፓርቲ ባለፈው እሑድ ምሽት በቻናል ዘጠኝ ቴሌቪዥን የቀረበውን የኃይል ሚዛን ማዛቢያ የአባላት ምልመላ አስመልክቶ የገጽታ ግንባታ ላይ እያተኮረ ነው።
የቪክቶሪያ ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ይህንኑና ሌሎች ተካታች ጉዳዮችን አካትቶ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
በአንቶኒ ባይረን መል ዕክቶች የቀድሞ የሌበር መሪ ቢል ሾርተን፣ የቪክቶሪያ ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ፣ የፌዴራል ፖለቲከኞች ማይክል ዳንቢ፣ አንድሩ ግሪፊንና ሳም ዳስትያሪ የከረረ ትችት ገጥሟቸዋል።
አቶ ባይረን ምንም እንኳ የተዛቡ መረጃዎች እየተሰራጩ ያሉ ቢሆንም፤ አተያያቸው ላይ ፅኑ አመኔታ እንዳላቸው ተናግረዋል።
የሕንድ ተቃውሞ
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ኒራንዳ ሞዲ ከቻይና ጋር በተፈጠረ የድንበር ግጭት ሳቢያ 20 ወታደሮቻቸው ሕይወታቸውን ቢያጡም፤ አገራቸው ሰላም ፈላጊ መሆኗንና ስትነካም የአጸፋ ምላሽ የምትሰጥ መሆኑን ገለጡ።
የሕንድ የጸጥታ ኃይሎች እስካሁን በሁለቱም ወገኖች በኩል የተከፈተ አንድም ተኩስ አለመኖሩን ሲገልጡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የድንበሩ አካባቢ ተረጋግቶ ያለ መሆኑን አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሞዲ ከቻይና ጋር በተፈጠረው የድንበር ግጭት ሕይወታቸው ያለፈውን የሕንድ ወታደሮች ዘክረዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዛዎ ሊያን በበኩላቸው ግጭቱ የተቀሰቀሰው የሕንድ ወታደሮች የድንበር መስመር በማለፋቸውና ቻይናውያን ወታደሮች ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
ይሁንና አቶ ሞዲ በሕንድ በኩል የተካሔደ የጠብ ጫሪነት ተግባር አልነበረም ሲሉ አስተባብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ሁለቱም ወገኖች ስክነትን እንዲላበሱ አሳስቧል።
ፓኪስታን - ሕንድ
የፓኪስታን መከላከያ ከሕንድ ጋር ተዘውትሮ የተኩስ ልውውጥ በሚካሔድባት ካሽሚር በተነሳ ግጭት አራት ሰዎች መሞታቸውን አስታወቀ።
ፓኪስታን ለግጭቱ መቀስቀስ የሕንድ ወታደሮችን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን፤ ሁነቱንም "ትንኮሳ አልባ የተኩስ አቁም ስምምንት ጥሰት" ብላዋለች።
ሕይወታቸው ያለፈው አራቱ ግለሰቦች ሰላማዊ ሰዎች እንደሆኑና አንድ ግለሰብም መቁሰሉ ተነግሯል።
ክስተቱን ምክንያት በማድረግም ፓኪስታን ጦሯን ወደ አካባቢው ልካለች።
ዩናይትድ ስቴትስ ፖሊስ
የ27 ዓመቱን አፍሪካዊ - አሜሪካዊ ሬይሻርድ ብሩክስን በአንድ ሬስቶራንት አካባቢ የገደለው ፖሊስ ጋሬት ሮልፍ የግድያ ክሶች ተመሰረቱበት።
ግለሰቡ ከአትላንታ ፖሊስ ሠራዊት አባልነት የተባረረ ሲሆን በ11 ክሶች ተጠያቂ ሆኗል።
የፉልተን ዐቃቤ ሕግ ፖል ሐዋርድ፤ ጋሬት ሮልፍ ተኩስ ከፍቶ አቶ ብሩክስን ለሞት በዳረገበት ምሽት በሕይወቱ ላይ የተቃጣ አስጊ አደጋ አልነበረም ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት - ዘርና ፖሊስ
የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባላት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፖሊስ እጆች ሕይወታቸው ያለፈ የአፍሪካውያን-አሜሪካውያንን ሞቶች አስባብ አስመልክቶ ምርመራ እንዲካሔድ ለተወጠነው ዕቅድ ድጋፋቸውን ሰጡ።
የአፍሪካ አገራት የሟቹን አፍሪካዊ-አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ወንድም ለከት ያለፈ የፖሊስ ኃይል አጠቃቀምና የዘር መድልዖዎን አስመልክቶ ትኩረት እንዲሰጥ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ የአፍሪካ አገራት አስቸኳይ ውይይት እንዲካሔድ ጠይቀዋል።
በሌላም በኩል የአውሮፓ ሕብረትን ወክለው የክሮኤሽያ አምባሳደር ቬስና ባቲስቲክ ኮስ "በዘረኝነትና ጥላቻ መንፈስ ተቀስቅሰው የሚካሔዱ አመፆች በሁሉም ክፍላተ ዓለማት አሉ። ራሳችንን ወደ ውስጥ መመልከት ይገባናል። ለዚያም፤ ያልታከቱ ጥረቶችና እርምጃዎችን መውሰድ ግድ ይለናል" በማለት ልብ አሰኝተዋል።

