ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ ከእንግሊዙ ቻርልስ ሳልሳዊ ጋር ለመጀመሪያ ተገናኙ።
አቶ አልባኒዚ የዳግማዊት ኤልሳቤጥ ሕልፈተ ሕይወትን አስመልክተው በአውስትራሊያውያን ስም ሐዘናቸውን ለንጉሥ ቻርልስ ገልጠዋል።
አውስትራሊያውያን ለንግሥቲቱ መልካም አተያይ እንዳላቸው፣ ጥልቅ ሐዘን የተሰማቸው እንደሆነና ለንግሥቲቱ የ70 ዓመታት አገልግሎትም ከፍ ያለ ከበሬታ እንዳለቸው ተናግረዋል።
ይሁንና አቶ አልባኒዚ በሐዘን ላይ ላሉት ንጉሥ ቻርልስ የአውስትራሊያውያንን የሪፐብሊክ ንቅናቄ ጉዳይ አላነሱም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ አውስትራሊያ ከእንግሊዝ ዘውዳዊ ሥርዓት ጋር ትስስሮሿን በጥሳ የሪፐብሊክ ሥርዓት እንድታቆም ከሚሹት የሪፐብሊካን ንቅናቄ ደጋፊዎች አንዱ ናቸው።
ንጉሥ ቻርልስ ከአቶ አልባኒዚ በተጨማሪ የጋራ ብልፅግና አገራት መሪዎች የካናዳውን ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ፣ የኒውዚላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደንና የባሃማስ ጠቅላይ ሚኒስትር ፊሊፕ ዴቪስን ተቀብለው አነጋግረዋል።
በሌላም በኩል የእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ለንግሥት ኤልሳቤጥ ቀብር ሥነ ሥርዓት ለንደን ከሚገኙት የአውስትራሊያና የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትሮችን በገጠር ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ወ/ሮ ትረስና አቶ አልባኒዚ በሁለቱ አገራት መካክል ስላለው የንግድ ስምምነት አንስተው ተናጋግረዋል።
ሁለቱ አገራት $3.9 ቢሊየን ዶላርስ [[2.3 ቢሊየን ፓውንድስ]] ግምት ያለው የንግድ ውል ተፈራርመዋል።