አውስትራሊያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ቀን ውስጥ ከ4,000 በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 መጠቃታቸው ተመዘገበ።
ለወረርሽኙ ሰፍቶ መዛመት የቪክቶሪያ የተማሪዎች ካምፕ ጉዞና የኒው ሳውዝ ዌይልስ የዓመቱ የትምህርት ጊዜ ማብቂያ ሽርሽር ተጠቃሽ ሆኗል።
ቅዳሜ ዕለት በመላው አውስትራሊያ 4,110 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁ ሲሆን ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ ብቻ 2,482 ተጠቅዋል፤ ቪክቶሪያ ውስጥ 1,504 ሰዎች ተይዘዋል።
ቪክቶሪያ ውስጥ በዛሬው ዕለት 1,240 በኮሮናቫይረስ የተጠቁ ሲሆን አራት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ኒው ሳውዝ ዌይልስ ውስጥ በዛሬው ዕለት 2,566 ሰዎች በቫይረስ ተይዘዋል።
ይህንኑ አስመልክተው የተላላፊ በሽታዎች ተጠባቢ ፕሮፌሰር ካትሪን ቤኔት የኦሚክሮን ኮሮናቫይረስን ለመግታት ጠቃሚው ስትራቴጂ ክትባት መከተብ መሆኑን አሳበዋል።
ወልዲያና ቆቦ
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንዳስታወቀው የሰሜን ወሎ ዋና ከተማ የሆነችውን ወልዲያን ጨምሮ የተለያዩ ከተሞች በመንግሥት ቁጥጥር ስር ውለዋል።
በዚህም መሠረት፤
- ወልዲያ፣ ሃራ፣ ሳንቃ፣ ስሪንቃ፣ ጎብዬ፣ ሮቢትና ቆቦ
- የኀሙሲት፣ እስታይሽ፣ አሁን ተገኝ፣ ድልብ፣ ኩል መስክና አካባቢያቸው በመንግሥት እጅ መግባታቸው ተገልጧል።
በሕወሓት በኩል ከተሞቹን ተዋጊዎቹ ለቅቀው እንደወጡ አስታውቋል።

