በኮሮናቫይረስ ሜልበርን ውስጥ አገርሽቶ መዛመት ሳቢያ የቪክቶሪያ መንግሥት በወሰደው እርምጃ ከጁላይ 4 ጀምሮ ለሁለት ሳምንታት የሰሜን ሜልበር የጋርዮሽ ቤት ነዋሪዎች ለቤት ውስጥ ቆይታ ግድ ተሰኝተው ቆይተዋል።
ከትናንት ቅዳሜ ማታ ጀምሮ ጥብቅ ገደቡ የላላላቸው የ33 አልፍሬድ ጎዳና ነዋሪዎች እንደተቀሩት ሜልበርናውያን ለምግብና አስፈላጊ ቁሳቁሶች ሸመታ፣ ለሕክምና፣ ለአካላዊ እንቅስቃሴ፣ ለሥራ ወይም ለትምህርት ወደ ደጅ መውጣት ይችላሉ።
ይሁንና በቫይረሱ የተያዙ ወይም ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው አንድ ሶስተኛ ያህሉ ነዋሪዎች በምርመራ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸው እስኪረጋገጥ ድረስ በመኖሪያ ቤታቸው ይቆያሉ።

በርካታ የአልፍሬድ ጎዳና የጋርዮሽ መኖሪያ ነዋሪዎች የጤና፣ ስነ ልቦናና የሥራ ድጋፍ እንደሚሹ ተናግረዋል።
የቪክቶሪያ ዕምባ ጠባቂ የአልፍሬድ ጎዳናና ሌሎች ስምንት የጋርዮሽ መኖሪያ ነዋሪዎችን ጨምሮ ጁላይ ውስጥ ለአምስት ቀናት ከቤት ውጪ እንዳይንቀሳቀሱ በተደረጉበት ወቅት የክብካቤ ይዘቶቹ ምን ያህል ሙሉዕ እንደነበሩ እየመረመረ ይገኛል።
ከነዋሪዎቹ ጋር በተደረጉት ንግግሮች የምግብና አስፈላጊ የሕክምና አቅርቦት፣ አካላዊ እንቅስቃሴ የማድረግ፣ የውጪ አየር ማግኘትና ክብካቤ ጉድለት ተደጋግመው ተነስተዋል።

