የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ በተለያዩ ፖሊስ መምሪያዎች ተዘዋውሮ በእስር ላይ ያሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባሎች የእስር ሁኔታን የመረመረ መሆኑን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ቀደም ሲል ረዘም ላሉ ጊዜያት ካደረጋቸው ክትትሎች በተጨማሪ ከፓርቲው እና ከእስረኞች ቤተሰቦች በቀረቡ አቤቱታዎች መነሻነት ከመጋቢት 1 እስከ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በቡራዩ ከተማ፣ በገላን ከተማ እና በሰበታ ፖሊስ መምሪያዎች በአካል በመገኘት ክትትል በማድረግ እስረኞችን፣ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎችን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተወካዮችን በማነጋገር ምርመራ ማካሔዱን ገልጧል።
በተለያዩ ጊዜያት እስረኞቹን በሚመለከት በፍርድ ቤት እና በዐቃቤ ሕግ የተሰጡ ውሳኔዎችን እና ትዕዛዞችን እንዲሁም የሕክምና ሰነዶችን መመልከቱንም አክሏል።
አያይዞም ስለጎበኛቸው እስረኞች አንስቶ፤ በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ በእስር ላይ የነበሩ አቶ ሚካኤል ጎበና፣ አቶ ኬኔሳ አያና፣ ዶ/ር ገዳ ወልጅራ፣ አቶ ዳዊት አብደታ፣ አቶ ለሚ ቤኛ፣ አቶ ገዳ ገቢሳ የተባሉ የፓርቲው አመራር መሆናቸውን የገለጹ ስድስት እስረኞችን እንዳነጋገርና በታካይነትም፤ ኮሎኔል ገመቹ አያና በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል፣ እንዲሁም አቶ አብዲ ረጋሳ ገላን ከተማ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ከቤተሰብ እና ከጠበቆቻቸው መረዳት መቻሉን አስታውቋል።
በሌላም በኩል፤ አቶ በቴ ኡርጌሳ በእስር ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት በፖሊስ ዋስትና ተፈቅዶላቸው በአንድ የሕክምና ተቋም ሕክምና ላይ የነበሩ መሆኑን ኮሚሽኑ መመልከቱን ገልጧል።
የኮሚሽኑ የምርመራ ግኝቶችም ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደላቸው፣ የክስ መዝገቦቻቸው ተዘግተው በፍርድ ቤት ውሳኔ በነፃ የተሰናበቱ፣ ምንም አይነት ክስ ያልተመሰረተባቸው እና ዐቃቤ ሕግ ክስ የማይመሰርትባቸው መሆኑን በማረጋገጥ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ፤ሆኖም ከወራት እስከ 2 ዓመት ለሚሆን ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙና የተወሰኑትም በእስሩ ሂደት በተፈጸመ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እና ድብደባ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶችና የጤና እክል የተጋለጡ እስረኞች መሆናቸውን እንዳመለከተ አስረድቷል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የኦነግ ፓርቲ አመራሮች ለተራዘመ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ እና ለደረሰባችው ጉዳት ሊካሱ የሚገባ ሲሆን፤ በተጨማሪም የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ እየተጣሰ እስረኞቹ ከሕግ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ስለሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል” ብለዋል፡፡

