ዛሬ ጥቅምት 8 ረፋዱ ላይ የኢትዮ ቴሌኮም አዳዲስ ፕሮጀክቶች በቅርቡ ይፋ በተደረገው የሳይንስ ሙዚየም ለጋዜጠኞች ዕይታ ቀርበው ነበር።
በዚህ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም የደምበኞች አገልግሎትን በተለያዩ አማራጮች ማግኘት የሚያስችለውን የኮንታክት ሴንተር መፍትሄ አስጀምሯል።
አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ደንበኞችን በድምፅና በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በተናጠል ያስተናግዱ የነበሩ የጥሪ ማዕከሎችን አሰራር ያዘመነና በልዩ ልዩ አማራጮች የሚቀርቡ የደምበኞችን ጥያቄ በአንድ ላይ አቀናጅቶ ለኮንታክት ሴንተር ወኪሉ በማቅረብ የቢዝነስ ተቋማት ለደምበኞቻቸው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ነው ተብሏል።
አገልግሎቱ በአምስት ቋንቋዎች ለተገልጋዩ ተደራሽ የሚሆን ሲሆን በተለያዩ ማህበራዊ ትስስር ገጾች የተጠየቁትን ጥያቄዎች ሰብስቦ በአንድ ቋት ለተቋሙ በማድረስ የተገልጋዩን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል የደምበኞች አገልግሎት ነው።
ከዚህ ቀደም የነበረው የኮንታክት ሴንተር አገልግሎት ድምፅ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ቢሆንም በአዲሱ ክላውድ ቤዝድ ኮንታክት ሴንተር ግን በሁሉም የማህበራዊ ትስስር ገጾች አገልግሎቱን ተቋማት ለደምበኞች ማድረስ ይችላሉ ተብሏል።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ለጋዜጠኞች እንዳብራሩት መሠል የአገልግሎቶች ሀገሪቱ እየገነባች ለምትገኘው የዲጂታል ኢኮኖሚ የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል።
አገልግሎቱ ከዚህ ቀደም ደምበኞች ወደ ጥሪ ማዕከል ደውለው ወረፋ በመጠበቅ የሚያጠፉትን ጊዜም በመከላከልና ደምበኞች በፈለጉት ጊዜ መጠቀም ይችላሉ።
እንደ ፍሬሕይወት ገለፃ ኢትዮ ቴሌኮም በዓለም ላይ የቴሌኮም አገልግሎት ከሚሰጡ 780 ኦፕሬተሮች መካከል 23ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ ደግሞ ከናይጄሪያ ቀጥሎ በ2ኛ ደረጃ ይገኛል ብለዋል።
[ ደመቀ ከበደ ፡ አዲስ አበባ]