ለ2020 የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው ከዕጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ጋር በምክትል ፕሬዚደንትነት እንዲወዳደሩ የታጩት ሴናተር ካማላ ሃሪስ፤ ዕጩነታቸውን በዛሬው ዕለት በይፋ ተቀብለዋል።
በምክትል ፕሬዚደንት ዕጩነት አቀባበል ልዩ ሥነ ሥርዓት ላይ ባደረጉት ንግግራቸው እንደ ቀድሞዎቹ ፕሬዚደንቶች ቢል ክሊንተንን፣ ባራክ ኦባማና ዕጩ ፕሬዚደንት ሂላሪ ክሊንተን ሁሉ የፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕን የአመራር ክሽፈት ነቅሰው የከረረ ትችት ሰንዝረዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ዕጩ ምክትል ፕሬዚደንቷ የዶናልድ ትራምፕ ክሽፈት ለሕይወቶች ቅጥፈትና ለኑሮዎች ፅልመት አስባብ መሆኑን ጠቅሰው "ኃዘኖቻችንን ወደ ፖለቲካ መሣሪያነት የለወጡ" ናቸው ሲሉም ብርቱ ክስ አቅርበውባቸዋል።
በአንፃሩም "ጆ ተግዳሮቶችን ወደ መርህነት ይቀይራሉ" በማለት ዲሞክራት ፓርቲን ወክለው የዩናይትድ ስቴትስ 46ኛው ፕሬዚደንት ለመሆን በዕጩነት የቀረቡትን ጆ ባይደንን የአመራር ብቃት በማንጸሪያነት አመላክተዋል።
ሴናተር ሃሪስ የእናታቸውን ከሕንድና የአባታቸውን ከጃማይካ መምጣት አንስተውም የዕሳቸው ምክትል ፕሬዚደንት ሆኖ መመረጥ ለመጤዎችና ጥቁር ሴቶች ታሪካዊ ወቅት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
ተጨማሪ ያንብቡ

ካማላ ሃሪስ የዲሞክራት ፓርቲ ዕጩ ምክትል ፕሬዚደንት ሆኑ
ከእሳቸው ትውልድ በፊት ለምርጫ ነፃነት የታገሉ ሴቶች ውለታ እንደሚገባቸው ጠቅሰው፤ የትግል አስተዋፅዖዎቻቸውን በንግግራቸው ሞገስ አላብሰዋል።
በነገው ዕለትም ፕሬዚደንት ትራምፕን ኖቬምበር 3 በምርጫ ሳጥን ድምፅ የሚፋለሙት ዕጩ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ዕጩነታቸውን መቀበላቸውን በልዩ ሥነ ሥርዓት በይፋ ይገልጣሉ።
በዛሬው ዕለት ጆ ባይደንን ለፕሬዚደንት፤ ካማላ ሃሪስን ለምክትል ፕሬዚደንትነት ሙሉ ድጋፋቸውን በመስጠት ንግግር ካደረጉት ውስጥ በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ የመጀመሪያው ጥቁር ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አንዱ ናቸው።
የንግግራቸው ይዘትና ግዝፈት ማዕከል የሆኑትን የዲሞክራሲ ዕሴቶች አጉልተው ለማንፀባረቅና ልብ ለማሰኘት የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ትውልድ ሥፍራ ፊላዴልፊያ ድረስ የተጓዙት ባራክ ኦባማ በንግግራቸው ወቅት "ክብርን የተመላው መልካም ስማችን በመላው ዓለም ጠልሽቷል፤ ዲሞክራሲያዊ ተቋማቶቻችን ከቶውንም አደጋ ተጋርጦባቸዋል" በማለት አሜሪካውያን ከመቼው ይበልጥ የልዕልናቸው መሠረት የሆነውን ዲሞክራሲ ጠብቆ ለማቆየት ድምጻቸውን ለጆ ባይደንና ዲሞክራት ፓርቲ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

Former President Barack Obama Source: SBS
እንዲሁም፤ የዲሞክራት ፓርቲ ከፍተኛ አባላት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ፣ የ2016 የዲሞክራት ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚደንት ሂላሪ ክሊንተንና የማሳቹሴትስ ሴናተር ኤሊዛቤት ዋረን የድጋፍ ድምጻቸውን ለጆ ባይደንና ካማላ ሃሪስ ቸረዋል።

Nancy Pelosi (L), Hillary Clinton (C) and Elizabeth Warren (R) Source: SBS
በኮሮናቫይረስ ሳቢያ የዘንድሮው የዲሞክራት ፓርቲ የዕጩነት ቅበላ ሥነ ሥርዓት የተካሄደው እንደ ቀድሞው ሺህዎች በታደሙበት አዳራሽ ውስጥ ሳይሆን በቀጥታ የኦንላይና ቴሌቪዥን ስርጭት ነው።
ሕዳሴ ግድብ - የገቢ ስብስብ
የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር ውኃ ሙሌት ሐምሌ 12 መጠናቀቅን ተከትሎ 116 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽ/ቤት ትናንት ይፋ አድርጓል።
ለግድቡ ሥራ በስኬት መጠናቀቅ የመንግሥት፣ የግል ተቋማት፣ የማኅበረሰብ አባላትና በውጭ አገር ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከፍ ያለ አስተዋፅዖ እያካሄዱ መሆናቸውን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ ገልጠዋል።
ባለፈው ሐምሌ ወር ብቻ 116 ሚሊዮን 473 ሺህ 348 ብር፤ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስካሁን በአጠቃላይ 13 ቢሊዮን 800 ሚሊዮን ብር ከሕዝብ ተሰብስቧል።
ቪክቶሪያ - ቫይረስ
ቪክቶሪያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ መስፋፋት እየቀነሰ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት 240 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
13 ሰዎች ለሕልፈተ ሕይወት ተዳርገዋል።
ምንም እንኳ የቫይረሱ ማሽቆልቆል አበረታች ቢሆንም የደረጃ 4 የኮሮናቫይረስ ገደቦችን ለማላላት ጊዜው ገና መሆኑን ፕሪሚየር ዳንኤል አንድሩስ ተናግረዋል።