የአል-ሻባብ ሚሊሺያ አባላት በሞቃዲሾ ሃያት ሆቴል ባደረሱት ጥቃት የስምንት ያህል ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው የፀጥታ ኃይል አዛዥ አስታወቁ።
ጥቃቱን የሰነዘሩትም በሁለት መኪኖች ላይ ተጠምደው የነበሩት ፈንጂዎች ፍንዳታ ተከትሎ ታጣቂ የሚሊሺያ አባላት ወደ ሆቴሉ ዘልቀው ተኩስ በመክፈት ነው።
ቡድኑ ባወጣው መግለጫም ታጣቂዎቹ ሃያት ሆቴል ውስጥ በነበሩት ሰዎች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን በመግለጥ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን ወስዷል።
የሶማሌ ወታደሮች ከሚሊሺያ አባላቱ ጋር መታኮሳቸውም ተነግሯል።
የሶማሊያ ምክር ቤት አባላትና የመንግሥት ባለስልጣናት ሞቃዲሾ ውስጥ ታዋቂ የሆነው ሃያት ሆቴል አዘውታሪ ተጠቃሚዎች ናቸው።
ሕይወታቸው ካለፉት ወይም ከቆሰሉት ውስጥ የመንግሥት ባለስልጣናት ይኑሩ አይኑሩበት እስካሁን አልተገለጠም።
አል-ሻባብ የሶማሊያን መንግሥት በኃይል አስወግዶ ስልጣን ለመያዝ ከአንድ አሠርት ዓመት በላይ ጥቃት በመሰንዘር ላይ ይገኛል።
***
በድርቅ ሳቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያና ሶማሊያ ውስጥ 22 ሚሊየን ሰዎች በቂ ምግብ ባለማግኘት ለፅኑዕ ረሃብ እንደሚጋለጡ የዓለም ምግብ ፕሮግራም አሳሰበ።
ምግባረ ሰናይ ድርጅቱ አክሎም፤ በድርቅ የተጠቁ አካባቢ ነዋሪዎች የቁም ከብቶች እየሞቱ እንደሆነ፣ ብርቱ የውኃና ምግብ እጥረት ገጥሟቸው እንዳለም አመልክቷል።
አያይዞም፤ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ሰዎች ቀዬዎቻቸውን ለቅቀው በተጨናነቁ የመጠለያ ካምፖች ውስጥ እንደሚገኙና የረድዔት ድርጅቶችም አስፈላጊውን አቅርቦት አሟልቶ ለማቅረብ ታውከው እንዳሉ ገልጧል።