በኢትዮጵያና ኬንያ አስተናጋጅነት ቻይና መራሽ የሰላም ጉባኤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊካሔድ ነው።
በአፍሪካ ቀንድ ላይ የሚያተኩረው የሰላም ጉባኤ በ2022 አጋማሽ ላይ የሚካሔድ መሆኑን ባለፈው ፌብሪዋሪ የተሰየሙት የቻይና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሹ ቢንግ ትናንት ቅዳሜ ናይሮቢ በሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ልዩ ልዑኩ በአፍሪካ ቀንድና በቻይና መካከል ያለው ግንኙነት የቆየና ስትራቴጂካዊ ሽርክናን የተላበሰ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አያይዘውም፤ በአካባቢው የድንበር፣ የጎሣና የሃይማኖት ግጭቶች ያሉ መሆኑን ያመላከቱት አቶ ሹ የሰላምና ፀጥታ መስፈን ጠቀሜታንም አንስተው ቻይና ልዩነቶች በምክክርና ድርድር እንዲፈታ የምትሻ መሆኑን ተናግረዋል።
ልዩ ልዑክ ሹ ቢንግ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ኬን ያን የጎበኙ ሲሆን፤ በቀጣይነትም ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳንን ይጎበኛሉ።
በሌላም በኩል፤ አምባሳደር ዴቪድ ሳተርፊልድን ጃኑዋሪ ላይ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አድርጋ የሰየመችው ዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን "በአፍሪካ ቀንድና አካባቢው በመካሔድ ላይ ያሉት የፖለቲካ፣ ፀጥታና ሰብዓዊ ተግዳሮቶች የዩናይትድ ስቴትስን ያልተቋረጠ ትኩረት ይሻል" ብለዋል።
ምርጫ ደቡብ አውስትራሊያ
ተሰናባች የደቡብ አውስትራሊያ ፕሪሚየር ትናንት ቅዳሜ ማርች 19 በተካሔደው የደቡብ አውስትራሊያ ምርጫ የመንግሥታቸውን ድል መነሳት ተከትሎ ከሊብራል ፓርቲ መሪነታቸው እንደሚለቁ አስታወቁ።
አቶ ማርሻል ትናንት ማምሻውን በምርጫው በለስ ያልቀናቸው መሆኑን አስመልክተው ሲናገሩ "በምርጫው ውጤት ደስተኛ አይደለሁም። ይሁንና ሙሉ ኃላፊነትን እወስዳለሁ። የሕዝብን ፈቃድ እቀበላለሁ" ብለዋል።
አክለውም የደቡብ አውስትራሊያ 46ኛው ፕሪሚየር ሆነው ለማገልገል በመታደላቸው ትልቅ ክብር የሚሰማቸው መሆኑንና በዳንስታን ምክር ቤት አባልነታቸው በመቀጠል አገልግሎታቸውን መስጠት እንደሚሹም ገልጠዋል።

ይሁንና የሌበር ፓርቲን ወክለው የዳንስታን ምክር ቤት ወንበር ዕጩ ሆነው ከቀረቡት ክሬሲዳ ኦሃንሎን ጋር ከሕዝብ ያገኙት ድምፅ በእጅጉ ተቀራራቢ በመሆኑ፤ ከቶውንም በሌበር ፓርቲ ተረትተው ወንበራቸውንም ሊያጡ እንደሚችሉ ግምት አለ።
ተሰናባቹ ፕሪሚየር ፓርቲያቸው ስብሰባ አካሂዶ ተተኪያቸውን እስኪመርጥ ድረስ በአመራር ኃላፊነታቸው ይቆያሉ።
በሌላ በኩል አዲሱ ተመራጭ የደቡብ አውስትራሊያ 47ኛ ፕሪሚየር ፒተር ማሊናዩስካስ ጤናን ማዕከል ያደረገ ሰፊ የድኅረ-ወረርሽኝ ፖሊሲ ግብር ላይ ለማዋል መወጠናቸውን አስታውቀዋል።

አያይዘውም፤ ማንም ይመረጥ ማን ከወደፊቱ የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተባብረው እንደሚሠሩ አመላክተዋል።
ሆኖም፤ ለደቡብ አውስትራሊያ የማይበጅ ከሆነ አሌ ሊሉ እንደሚችሉ አሳስበዋል።
ሌበር ራሱን ችሎ አብላጫ የምክር ቤት አባላት ያሉት መንግሥት ለማቆም የሚያሻው 24 የምክር ቤት ወንበሮች ሲሆኑ 25 የተረጋገጡ 2 የማሸነፍ ተስፋ የተጣለባቸው ወንበሮችን በማግኘት 27 የምክር ቤት አባላት ያሉት መንግሥት ሊያቆም እንደሚችል ይጠበቃል።

