የግሪንስ ፓርቲ ሴናተር ከነበራቸው የፓርላማ ኃላፊነትና የፍቅር ግንኙነታቸው መስመሮች የሚጣረሱ በመሆኑና የፈፀሙት ተግባርም "ስህተት" መሆኑን አምነው በመቀበል ከፓርላማ ኃላፊነታቸው ለቅቀዋል።
ሆኖም፤ በግሪንስ ፓርቲ የነባር ዜጎች ጉዳይ ተጠሪነታቸው ይቀጥላሉ።
የሴናተር ቶርፕ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች ከአንድ በወንጀል ንኪኪ ተጠርጣሪ የሞተር ብስክሌት ቡድን የቀድሞ መሪ ጋር ያላቸው የፍቅር ግንኙነት ከፓርላማ የሕግ አስከባሪ ኮሚቴ አባልነታቸው ጋር እንደሚፃረር ቢነግሯቸውም ቸል ብለው የፍቅር ግንኙነታቸውን ቀጥለው ነበር።
ወ/ሮ ቶርፕ በአባልነት ያሉበት የፓርላማ ኮሚቴ የሞተር ብስክሌትና የተደራጁ የወንጀል ቡድኖችን አስመልክቶ ምስጢርነቱ ከፍ ያለ የመረጃ ማብራሪያን የሚያደምጥ ኮሚቴ ነው።
የሥራ አጥነት ቁጥር
የአውስትራሊያ ይፋ ሥራ አጥነት ቁጥር 3.5 ፐርሰንት ላይ ረግቷል።
የአውስትራሊያ ስታቲስቲክስ ቢሮ ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ባለፈው ወር 900 አዳዲስ ሥራዎች ተፈጥረዋል።
በሕመም ሳቢያም የሐኪም ፈቃድ በመውሰድ በሥራ ገበታቸው ላይ የማይገኙ ሠራተኞች ቁጥር ቀንሷል።
ይሁንና የሥራ ሚኒስትር ቶኒ በርክ፤ የሴፕቴምበር ወር የሥራ አጥነት ቁጥር የሚያሳየን በደመወዝ ዕድገትና በሥራ አጥነት ቁጥር ዝቅተኝነት መካከል ያሉት ግንኙነቶች አለመሰናሰላቸውን ነው ብለዋል።
የወቅቱ የአውስትራሊያ የደመወዝ አመላካች አሃዝ 2.6 ነው።