ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን እሳቸውና ባለቤታቸው የግብረ አካል ጉዳተኛ ባልሆኑ ሁለት ልጆች "መባረካቸውን" አስመልክተው መናገራቸው ብርቱ ትችት አስዘንዝሮባቸዋል።
አቶ ሞሪሰን ሁለት ልጆቻቸውን አንስተው መናገራቸው ጭብጣቸውን ለማስረዳት ሲሉ እንጂ በተቃራኒው አለመሆኑን ጠቅሰው ሰዎች በዚያ መልኩ እንዲረዷቸው አመላክተዋል። ይቅርታም ጠይቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለትችትና ይቅርታ ያጋለጠው የአራት ዓመት ኦቲዝም ተጠቂ ልጅ እናት የሆኑት ካትሪን ዮማን ትናንት ምሽት ብሪስበን በተካሔደው የመጀመሪያው የመሪዎች ክርክር ወቅት ተገኝተው ላቀረቡት ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ነው።
ወ/ሮ ዮማን ጥያቄያቸውን ለመንሳት ግድ የተሰኙት ልጃቸው 30 ፐርሰንት ወይም በሺህዎች የሚቆጠር የግብረ አካል ጉዳተኞች ድጎማ የተቀነሰበትና ገና ለየትኛው ፓርቲ ድምፃቸውን እንደሚሰጡ ከውሳኔ ላይ የደረሱ ባለመሆኑ ጭምር ነው።
የአቶ ሞሪሰን ምላሽ የዘንድሮው የዓመቱ አውስትራሊያዊና የግብረ አካል ጉዳተኛው ዲለን አልኮትንም "ለእኛና ለቤተሰቦቻችን ማዘን ምንም አይጠቅምም። የሚጠቅመው እኩል ክብካቤ ስናገኝና በሕይወታችን ላይ ቁጥጥር እንዲኖረን ምርጫ እንዲኖረን ማድረግ ሲቻል ነው" የሚል ምላሽ እንዲሰጥ ገፋፍቶታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩም አልኮትን በግል ይቅርታ ጠይቀዋል።
ወ/ሮ ዮማን አቶ ሞሪሰን ከመሪዎች የመጀመሪያው ክርክር በኋላ በግል እንዳነጋገሯቸው አንስተው ሆኖም ለጥያቄያቸው ቀጥተኛ ምላሽ እንዳልሰጧቸው ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቶች የሳቸውን ጥያቄ እንዲያደበዝዝ እንደማይሹም አሳስበዋል።
ትናንት ምሽት ላይ በሌበር መሪ አንቶኒ አልባኒዚና ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን መካከል በተካሔደው የመጀመሪያው የመሪዎች ክርክር አቶ አልባኒዚ 40፣ አቶ ሞሪሰን 35 ድምፆችን ከታዳሚዎች አግኝተዋል።

ድምፁን የሰጡት የትኛውን ፓርቲ እንደሚመርጡ ገና ከውሳኔ ላይ ያልደረሱና በመሪዎቹ ክርክር ላይ ታድመው ጥያቄዎችን በማንሳት ከክርከሩ ፍፃሜ በኋላ ለየትኛው ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት እንደወሰኑ ከተጠየቁት 100 ሰዎች ውስጥ ነው።
ክርክሩን ከተከታተሉት ውስጥ 25ቱ አሁንም ከውሳኔ ላይ አልደረሱም።
በክርከሩ ወቅት የግብረ አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ የምጣኔ ሃብት፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምስረታ፣ የቻይናና የድንበር ጥበቃ ጉዳዮች ሰፋ ያለ ክርክር ተካሂዶባቸዋል።

