የአልሻባብ ሚሊሺያ ቡድን አባላት በሞቃዲሾ ሃያት ሆቴል በሰነዘሩት ጥቃት ሳቢያ ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ወደ 20 ከፍ ማለቱና 40 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱ ተገለጠ።
ሆቴሉ በሶማሊያ ምክር ቤት አባላትና የመንግሥት ባለልጣናት የሚዘውተር ሲሆን፤ የሟቾቹና የቁስለኞች ማንነት እስካሁን ይፋ አልሆነም።
የተኩስ ጥቃቱ የጀመረው በሁለት መኪናዎች ውስጥ የተጠመዱ ፈንጂዎች ፍንዳታን ተከትሎ ነው።
የአልሻባብ ቡድን ከአልቃይዳ ጋር ትስስር ያለው ሲሆን ለጥቃቱም ኃላፊነቱን ወስዷል።
የፀጥታ ኃይል ባለስልጣናት ለአንድ ምሽት ሆቴሉንና ሰላማዊ ስዎችን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው የነበሩ ሚሊሺያዎችን ደምስሰው ሆቴሉንና አካባቢውን በቁጥጥራቸው ስር ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል ግና የፀጥታ ኃይላቱ አካክባቢውን ሙሉ ለሙሉ በቁጥጥራችው ስር ለማድረግ እየጣሩ መሆኑ ይነገራል።
***
የ24 ዓመቷ ሩዋንዳዊት ሊሊያን ሙጋቤካዚ ኦገስት 7 በፈረንሳዊው ሙዚቀኛ ታይክ ኮንሰርት ላይ በተገኘችበት ወቅት አለባበሷ ወግ የጠበቀ አይደለም በሚል ዘብጥያ ወርዳለች።
ሊሊያን በአለባበሷ ሳቢያ ክስ ተመስርቶባት ፍርድ ቤት በቀረበችበት ወቅት የዋስ መብት የተነፈጋት ቢሆንም ትናንት የዋስ መብቷ ተጠብቆ መለቀቋ ተነግሯል።
በአለባበሷ ምክንያት ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች ግና እስከ ሁለት ዓመት የሚደርስ የእሥር ብይን ሊጣልባት ይችላል።