የአውስትራሊያ ዓለም አቀፍ ድንበር ከዛሬ ሰኞ ፌብሪዋሪ 21 ጀምሮ ክፍት ሆኗል።
የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቶችን የተከተቡ የባሕር ማዶ መንገደኞች ከሁለት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አውስትራሊያ እንዲዘልቁ ተደርጓል።
ወደ አውስትራሊያ ዛሬ ማለዳ 6am ላይ የዘለቁት የመጀመሪያዎቹ ዓለም አቀፍ መንገደኞች ከሎስ አንጀለስ ተነስተው ሲድኒ አውሮፕላን ማረፊያ የደረሱት ሲሆኑ፤ እነሱንም ተከትለው የቶኪዮ፣ ቫንኮቨርና ሲንጋፖር መንገደኞች ሲድኒ ገብተዋል።
በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥም 56 ዓለም አቀፍ መንገደኞችን የጫኑ አውሮላኖች የአውስትራሊያ አውሮፕላን ማረፊያዎች ላይ ያርፋሉ፤ በቀጣዮቹ ቀናትም ወደ አውስትራሊያ የሚያቀኑ የዓለም አቀፍ በረራዎች ቁጥር ይጨምራል።
በወረርሽኙ ሳቢያ ዓለም አቀፍ በረራ በመዘጋቱ በየወሩ እስከ $3.6 ኒሊየን ዶላርስ የገቢ እጦት በንግድ ተቋማት ላይ አሳድሯል።
የዓለም አቀፍ በረራውን መከፈት አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን አንድ ቀን ቀደም ብለው ትናንት እሑድ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት "የመቆያ ጊዜ አልፏል። ሻንጣዎቻችሁን ሸክፉ። ገንዘቦችቻሁን ይዛችሁ መምጣታችሁን እንዳትዘነጉ፤ በርካታ የምታጠፉባቸው ሥፍራዎች አሉና" ብለዋል።
የኳንታስ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አለን ጆይስም በበኩላቸው "ለዚህ የበቃነው ምስጋና ይግባቸውና ክትባቶችን በተከተቡ በሚሊየን የሚቆጠሩ አውስትራሊያውን ምክንያት ነው" በማለት ክትባት የተከተቡ አውስትራሊያውያንን አመስግነዋል።
ንግሥት ኤልሳቤጥ
ንግሥት ኤልሳቤጥ በኮቪድ-19 ተጠቁ።
የባኪንግሃም ቤተመንግሥት እንዳስታወቀው የ95 ዓመቷ የእንግሊዝ ንግሥት 'መለስተኛ ጉንፋን መሰል ምልክቶች' የታየባቸው ሲሆን፤ በመጪው ሳምንት ወደ ቀላል ዕለታዊ የሥራ ገበታቸው ይመለሳሉ።

ንግሥቲቱ ባለፈው ሳምንት ከአልጋ ወራሻቸውና በኮቪድ 19 ከተጠቁት የዌልስ ልዑል ቻርልስ ጋር ተገናኝተው ነበር።

