ጆ ባይደን በ25 ሺህ ወታደሮች በታጠረ ብርቱ የጸጥታ ኃይል ተከበው የዩናይትድ ስቴትስ 46ኛው ፕሬዚደንት ሆነው ጃኑዋሪ 20 2021 ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡
ለዋሽንግተን ዲሲ በጦር ተሽከርካሪዎች መከበብና የኮንክሪት አጥር መታጠር ሰበብ የሆነው ጃኑዋሪ 6 በቀኝ ፅንፈኛ የቀድሞው ፕሬዚደንት ትራምፕ ደጋፊዎች ካፒቶል ሂል ላይ የደረሰው የአመፅ ተቃውሞ ነው፡፡
ከፀጥታው አስጊነት በተጨማሪም አለቅጥ ተስፋፍቶ ያለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ታድመው የቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ሊገኙ አልቻሉም፡፡
ፕሬዚደንት ባይደን በቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር አሜሪካውያን በአመፅ ፈንታ የሰላም መንገድን እንዲከተሉ አመላክተዋል፡፡
"በፖለቲካ ጎዳና ላይ እሳት ተላብሶ ሁሉንም ማውደም ግድ አይልም፡፡ እያንዳንዱ ልዩነት የጦርነት ሰበብ ሊሆን አይገባም፤ የፈጠራ ቅጥፈቶችንና የአስመሳይ ባሕልን የግድ አሌ ልንል ይገባናል" ሲሉም ጥሪ አድርገዋል፡፡
ካማላ ሃሪስም በበኩላቸው ቃለ መሃላ በመፈጸም በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴትና ጥቁር ምክትል ፕሬዚደንት ሆነዋል፡፡
ካማላ እናታቸው ሽያማላ ጎፓላን ሃሪስ ከሕንድ አባታቸው ዶናልድ ሃሪስ የጃማይካ መጤ ናቸው፡፡
በቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት ሌዲ ጋጋ የአሜሪካ ብሔራዊ መዝሙርን ዘምራለች፡፡

ሌላዋ ድምፃዊት ጄኒፈር ሎፔዝ በበኩሏ "This Land Is Your Land" & "America, The Beautiful" ጣዕመ ዜማ አቀንቅናለች፡፡

የ22 ኣመቷ ወጣት ባለ ቅኔ አማናዳ ጎርማን "The Hill We Climb" ቅኔ ዘርፋለች፡፡
'a nation, that isn't broken, simply unfinished'

ከቃለ መሃላው ሥነ ሥር ዓት በኋላ በቀጥታ ወደ ሥራ የተሰማሩት ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ፕሬዚደንታዊ ሥራ አስፈጻሚ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የኮሮናቫይረስ መከላከል ሥራ አፈጻጸም መመሪያ፣ ወደ ፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት መመለስና ዕገዳ ተጥሎባቸው የነበሩ የእስልምና እምነት ተከታይ አገሮች ዕገዳ ማንሳትን ጨምሮ 17 የሥራ አፈጻጸም መመሪያዎችን ፈርመዋል፡፡
ምክትል ፕሬዚደንት ሃሪስም በሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ተገኝተው ሶስት አዲስ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላትን ቃለ መሃላ አስፈጽመዋል፡፡
እንኳን ደስ ያለዎት
የቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎ የተለያዩ አገራት መሪዎች ለፕሬዚደንት ባይደንና ምክትል ፕሬዚደንት ሃሪስ የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክቶች ልከዋል፡፡
የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የአዲሱ አስተዳደር ለውጥ ለአሜሪካ ሁነኛ ወቅት ስለመሆኑ ሲያመለክቱ፤
"ጆ እና ካማላ ሃሪስን በዛሬዋ ዕለት ለደረሱበት ስኬት እንኳን ደስ ያላችሁ እላለሁ፡፡ ይህ ለአሜሪካ ማለፊያ ነገር ነው፡፡ በውዥቀት ላይ ለነበረች አገር ይህ አንድ እርምጃ ወደፊት ነው፡፡ ለእኛና ለአሜሪካ ትልቅ ወቅት ነው" ብለዋል፡፡
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን በበኩላቸው "የአውስትራሊያና ዩናይትድ ስቴትስ ወዳጅነት ከመቼውም በላይ አሁን ጠቃሚ ነው፡፡ ለሁለታችሁም በሥራ ዘመናችሁ ስኬትን እመኝላችኋለሁ፡፡ ከእናንተ አዲሱ አስተዳደር ጋር አብሬ ለመሥራት አሻለሁ" በማለት የመልካም ምኞት መግለጫቸውን ልከዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴም "በዚህ የታሪክ ሥሪ ወቅት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት፟አሜሪካዊትና የደቡብ እስያ ዝርያ ያላቸውን ምክትል ፕሪዘደንት ካማላ ሃሪስ እንኳን ደስ አለዎት ብያለሁ፡፡ ከዩናይትድ ስቴትስ ባሻገርም አያሌ ልጃገረዶችንና ሴቶችን መንፈስ እንደሚያነቃቁ ምንም ጥርጣሬ የለኝም፡፡ በሩ ተከፍቷል፤ በትልቁ ማለም ይችላሉ" ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ኡርሱላ ፎን ደር ላየን የዩናይትድ ስቴትስ ዲሞክራሲ ያሳየውን ፅናት አድንቀው፤ አውሮፓ ከዋይት ሃውስ ጋር በሉላዊ ጉዳዩች ተባብራ መሥራት እንደምትሻ ገልጠዋል፡፡
የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሄይኮ ማስ አዲሱ ፕሬዚደንት ለአሜሪካ እፎይታ እንደሆነ ለቻናል R-T-L ተናግረዋል፡፡

