የሽብር ብይን - ሜልበርን
ሜልበርን ፌዴሬሽን አደባባይ ላይ የሽብር ጥቃት በመወጠን ክስ የተመሰረተበት ግለሰብ የ10 ዓመት እሥራት ተበየነበት።
የቪክቶሪያ ፖሊስ በርካታ ወራትን የፈጀ ክትትል ካደረገ በኋላ አሊ ካሊፍ ሻየር አሊን በ2017 ለማሰር ችሏል።
አሊ - ሰባት ዓመት ተኩሉን ያለ ምህረት በፅኑ እሥራት እንዲያሳልፍ የተፈረደበት ሲሆን፤ ዕቅዱም "የተዛባ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ዓላማ"ን ዕውን ለማድረግ በ"ሽብርና ሰቆቃ" የተነደፈ ነበር ሲሉ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ጆን ቻምፒየን ተናግረዋል።

[[አሊ በ2018 መኪና ሙሉ የጋዝ ሲሊንደሮችን ጭኖ መኪናውን በርክ ጎዳና - ሜልበርን መሃል ከተማ ውስጥ ከማጋጨቱ በፊት ሶስት ሰዎችን የወጋውና የሻይ ቤት ባለቤት የነበሩትን ሲስቶ ማላስፒናን የገደለው ሐሰን ካሊፍ ሻየር አሊ ታናሽ ወንድም ነው።]]
ጋዝ ሪፖርት
የአከባቢያዊ ተፈጥሮ አንቂዎች የአውስትራሊያውያን ግብር ከፋዮች ንዋይ ለድኅረ ኮቪድ - 19 የምጣኔ ሃብት ማንሰራሪያ ታሳቢነት ግዙፍ ለሆነ የጋዝ ኢንዱስትሪ ሊውል መሆኑን የሚጠቁም ሾልኮ የወጣ ረቂቅ ሰነድን ተመርኩዘው ስጋት የገባቸውን መሆኑን ገለጡ።
ረቂቅ ዕቅዱ የተነደፈው መንግሥትን በሚያማክረው በኮቪድ - 19 ኮሚሽን በሚመራው የፍብረካ ግብረ ሃይል ነው።
ዕቅዱ ለጋዝ ኢንዱስትሪው መደጎሚያ እንዲሰጥ፣ የአካባቢ ተፈጥሮ ድንጋጌዎች እንዲላሉና የፕሮጄክት ይሁንታዎች እንዲፋጠኑ እንዲደረግ ጥሪ ያቀርባል።
የሎክ ዘ ጌት ኅብረት ጉዳይ አስፈጻሚ ቡድኗ ናኦሚ ሆጋን ረቂቁ በእጅጉ ያሳሰባቸው መሆኑን ሲገልጡ፤
"የጋዝ ኢንዱስትሪ ሰዎች በአውስትራሊያ ግብር ከፋዮች ንዋይ ደጓሚነት ለወደፊት የጋዝ መሠረተ ልማታቸው እንዲከፈልላቸው ዕቅዳቸውን ሲገፉ ማየቱ በእጅጉ ስጋት አሳዳሪ ነው። የአውስትራሊያን የውስጥ የኢነርጂ አቅርቦት እንደማያሳድግ እንረዳለን። ርካሹ ንፋስ፣ በባትሪ የሚታገዝ ሶላርና በውኃ ኃይል የሚገፋ ሃይድሮ መሆኑን እናውቃለን" ብለዋል።
የኃይል ምንጫ ፍኖተ ካርታ
የኢነርጂ ሚኒስትር አንገስ ቴይለር የተፈጥሮ ጋዝን ጨምሮ ለአውስትራሊያ የኃይለ ምንጭ በቀዳሚነት ሊውሉና ጠቀሜታ አሏቸው ያሉትን ረቂቅ ዕሳቤዎች ያቀፈ ፍኖተ ካርታ ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
የቴክኖሎጂ ሙዋዕለ ንዋይ ፍኖተ ካርታው ታዳሽ ኃይል፣ ባዮፊዩል፣ ሃይድሮጂንና ኑክሊየር ቴክኖሎጂዎችን አክሎ 140 የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቶችን አካትቷል።
ፍኖተ ካርታው ታዳሽ ኃይል፣ ንፋስና ሶላር ርካሽ ቢሆኑም አስተማማኝ እንዳልሆኑ ጠቁሟል።
ይሁንና የአየር ንብረት መማክርት ጉባኤ ፍኖተ ካርታው ላይ የሰፈሩትን አስተሳሰቦች በመቃወም ንፋስና ሶላር ርካሽ የኃይል ምንጭ እንደሆኑና በባትሪዎች ሲደገፉም አስተማማኝ መሆናቸውን አስረድቷል።
የቤት ውስጥ አመፅ
የኒው ሳውዝ ዌይልስ ፖሊስ በምዕራብ ሲድኒ ቤታቸው ውስጥ ሚስቱን ወግቶ የገደለውን የ31 ዓመት ሰው በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ።
የ27 ዓመቷ ሴት በስለት ውግ እየተሰቃየች በመሆኑ ለፖሊስ ረቡዕ አመሻሽ 6.30 pm ላይ ኩዋከርስ ሂል ከፍተኛ እንዲደርስ ተደውሎ በሥፍራው ተገኝቷል።
ምንም እንኳ በሕክምና ግልጋሎት ሰጪዎች የ27 ዓመቷን ሴት ለማዳን ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም፤ ሕይወቷ እዚያው በተወጋችበት ሥፍራ አልፏል።
ባልና ሚስቱ አብረው ይኖሩ የነበረ ቢሆንም፤ ባልየው ቀደም ሲል በቤት ውስጥ አመፅ ሳቢያ የማገጃ ትዕዛዝ የወጣበት መሆኑን ፖሊስ ገልጧል።
ገዳዩ በብላክታውን ሆስፒታል የአዕምሮ ጤና ምርመራ የተደረገለት ሲሆን ሪቨርስቶን ፖሊስ ጣቢያ ቀርቦም ምርመራ ተካሂዶበታል።
እርስዎ መይም ሌላ የሚያውቁት ሰው ለቤት ውስጥ አመፅ የተዳረጉ ከሆነ 1800 RESPECT ((1800 737 732)) ይደውሉ። አስቸኳይ አደጋ ከሆነም 000 ይደውሉ።

