የአውስትራሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔኒ ዎንግ ከቻይናው አቻቸው ዋንግ ዪ ጋር ቤጂንግ ላይ የተገናኙት ረቡዕ ምሽት ሲሆን፤ ይህም ከአራት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው የአውስትራሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት ነው።
የሚኒስትሯ ጉዞ በቻይና አውስትራሊያ ላይ ተጥለው ያሉት ማዕቀቦች እንዲነሱና ቻይና ውስጥ በእሥር ላይ የሚገኙ ሁለት አውስትራሊያውያን ዜጎች እንዲለቀቁ ለማስቻል በር ከፋች ይሆናል የሚሉ ተስፋዎችን አሳድሯል።
ሴናተር ዎንግ በቤጂንግ ለ50ኛው የአውስትራሊያና ቻይና ዲፖማሲያዊ ግንኙነት በዓል በአካል መገኘታቸው ያስደሰታቸው መሆኑን ገልጠው፤
"በዚህች ታሪካዊ ቀን ይህ ግንኙነት እዚህ እንዲደርስ አያሌዎች አስተዋፅዖዎቻቸውን አበርክተዋል" በማለት ቀደም ሲል ከምሥረታው እስከ ዘለቄታው ልዩ ሚና ለተጫወቱ አውስትራሊያውያንና ቻይናውያን ዕውቅናን ቸረዋል።

አክለውም፤ ስለ ቻይናና አውስትራሊያ ግ ንኙነት ጠቀሜታ በማንሳት፤
"ከቻይና ጋር ያለንን ግንኙነት ማርጋት የአውስትራሊያ ጥቅም እንደሁ የምናምን መሆኑን መንግሥት ግልፅ አድርጓል። እንዲሁም የግንኙነቱ መርጋት ለቻይናም ጥቅም ጭምር መሆኑንም እንደምናምን ግልፅ አድርገናል። በአውስትራሊያና ቻይናና መካከል ሁሉን አካታች ስትራቴጂያዊ ወዳጅነት ለሁለቱ አገራት ትሩፋትን የሚያስገኝ የንግግርና ተሳትፎ ሥነ ጥበብ ነው ስንል አተያያችንን በመግለፁ እንቀጥላለን። ልዩነቶቻችንን በብልሃት መፍታት ከቻልን፤ የሁለትዮሽ ግኑኙነታችንን ማጎልበትና የጋራ ጥቅሞቻችንን ማስከበር ይቻለናል ስንል አተያያችንን በመግለፁ እንቀጥላለን። ይህ ትውልድ በብልሃት እንዲፈታው ገጥሞት ያለው ተግዳሮትም ይህ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

የቻይናው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው፤ አውስትራሊያና ቻይና መሠረታዊ የሆነ የጥቅም ግጭት እንደሌላቸው በመጠቆም ክብረ በዓሉን በማሰብ ግ ንኙነታቸውን ዳግም መቀጠል እንደሚገባቸው ገልጠዋል።

