ሲኔጋላዊው ሳዲዮ ማኒ ለሁለተኛ ጊዜ የዓመቱ የአፍሪካ ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች ሆኖ ተመረጠ።
ሴኒጋላዊው አጥቂ ለዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ እግር ኳስ ተጫዋች ሽልማት የበቃው ተፎካካሪዎቹ ሆነው ቀርበው የነበሩትን የግብፁን ሞ ሳላህ እና የአገሩን ልጅ ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋች ኢድዋርድ ሜንዲን ረትቶ ነው።
ሳዲዮ በአሁኑ ወቅት ለጀርመኑ ሻምፒዮን ባየር ሙኒክ ተጫዋችነት ኮንትራት ፈርሞ ይገኛል።
በዚህ ዓመት ሴኔጋልን ለአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊነት ያበቃችውን ወሳኝ ፍፁም ቅጣት ምት ለግብነት አስቆጥሯል፤ ሲልም ከስድስት ሳምንት በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ያስቆጠራት ግብ ሴኒጋልን ለዓለም ዋንጫ ተሳታፊነት አብቅታለች።
ሳዲዮ ሽልማቱን የተቀበለው በሞሮኮ መዲና ራባት በተካሔደ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝቶ ነው።
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚደንት ፓትሪስ ሞስቴፔ በዚህ ዓመት በኳታር በሚካሔደው የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ተወዳዳሪ የአፍሪካ ቡድናት ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ጋና፣ ቱኒዝያና ካሜሩን ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው የአፍሪካ ኩራት እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጠዋል።
አፍሪካዊቷ ቱኒዝያ ከአውስትራሊያ ሶኮሩስ ብሔራዊ ቡድን ጋር በአንድ ምድብ ውስጥ ተፎካካሪ ናት።