ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 12 ቀን 2015 መዲናይቱን አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍለ አገራት "ለኢትዮጵያ እቆማለሁ፤ ድምፄን አሰማለሁ" በሚል መሪ ቃል የድጋፍና ተቃውሞ ሰልፎች ተካሒደዋል።
በዕለቱ በተካሔዱት ሰልፎች ተሳታፊ የነበሩ ኢትዮጵያውያን "የሰላምና መረጋጋት ጊዜ ደርሷል"፣ "ኢትዮጵያ እንደ አገር እንድትቀጥል መስዋዕትነት የሚከፍለው መከላከያ ሠራዊት ክብር ይገባዋል"፣ የሚሉ መፈክሮችን ከፍ አድርገው በመያዝ ድጋፋቸውን የገለጡ ሲሆን፤ በሌላም በኩል "ኢትዮጵያ ሉ ዓላዊነቷን ለማስከበር የማንም ይሁንታ አያስፈልጋትም" በሚል "ምዕራባውያን ካልተገባ ጣልቃ ገበነት ተቆጠቡ" የሚሉ የተቃውሞ ድምፆችንም አስተጋብተዋል።
በሰልፎቹ ላይ የተለያዩ የመንግሥት ተጠሪዎችና የተቋማት ተወካዮች ተገኝተው ንግግር አሰምተዋል።
የሰላም ንግግር
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በአፍሪካ ኅብረት መሪነት በኢትዮጵያ መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ አስተዳደር መካከል ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚካሔደውን የሰላም ንግግር አገራቸው እንደምትደግፍ ትናንት ዓርብ ይፋ ባደረጉት መግለጫ ገለጡ።
አቶ ብሊንከን፤ በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ደቡብ አፍሪካ ይካሔዳል ተብሎ የሚጠበቀውን የስላም ንግግር አስመልክተው በፍጥነት የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ የኢትዮጵያና ኤርትራ መከላከያ ሠራዊቶችም በአስቸኳይ ከጥምር ማጥቃት ተገትተው ለሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ እንዲያደርጉ በማለት ዳግም ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ሁለቱ የሰላም ንግግር አካሂያጅ ወገኖች ለሰኞው ስብሰባ ነገ እሑድ ቀድመው ደቡብ አፍሪካ ከገቡ የአፍሪካ ኅብረት ባሰናዳው የእራት ግብዣ ላይ ተገናኝተው ይፋዊ ያልሆነ ንግግር እንዲያደርጉ የታሰበ መሆኑን ምንጮች ከወዲሁ ጠቁመዋል።