በ96 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የእንግሊዟን ንግሥትና የአውስትራሊያ ርዕሰ ብሔር ዳግማዊት ኤልሳቤጥን ለመዘከር ዛሬ በአውስትራሊያ ፓርላማ ታላቁ አዳራሽ ውስጥ ብሔራዊ የሐዘን ሥነ ሥርዓት ተካሂዷል።
በልዩ ዝከረ መታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱም ላይ ፖለቲከኞች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በሐዘን ሥነ ሥርዓቱ የአንድ ደቂቃ የሕሊና ተሃስቦ የተካሔደ ሲሆን፤ ጠቅላይ እንደራሴ ዴቪድ ሃርሌይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚና የተቃዋሚ ቡድን መሪ ፒተር ዳተን ንግግር አድርገዋል።
ጠቅላይ እንደራሴ ሃርሌይ "የዛሬዋ ዕለት የሐዘን ቀን ናት። ታሪክ ጥቂት እንደ ንግሥት ኤልሳቤጥ ያሉትን ያወሳል። ስለ ሕልፈተ ሕይወታቸው ስናዝን፤ ከእሳቸውን ድንቅ የሕይወት ትሩፋት ተቋዳሾችና እማኞች በመሆናችንም ውለታ ይገባናል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ በበኩላቸው በተለዋዋጩ ዓለም ንግሥቲቱ ለብዙዎች፣ ለረጅም ጊዜያት የዘለቄታ አስተማማኝ እንደነበሩ አንስተዋል።
የተቃዋሚ ቡድ መሪ ፒተር ዳተንም በበኩላቸው" ሐዘን ለፍቅር የሚከፈል ዋጋ ከሆነ፤ ባለፉት 14 ቀናት ውስጥ የመነጨው ሉላዊ ሐዘን ምን ያህል ተፈቃሪ እንደነበሩ የሚናገር ነው" ብለዋል።
በንግሥቲቲ ሕልፈተ ሕይወት ሳቢያ ለሁለት ሳምንታት የተዘጋው የአውስትራሊያ ፓርላማ በነገው ዕለት የጋራ የሐዘን መግለጫ ለማሳለፍ ልዩ ጉባኤ ይቀመጣል።