የሩስያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ለ300 ሺህ ተጠባባቂ ወታደሮቻቸውን ያደረጉት የክተት ጥሪ በዓለም መሪዎች ዘንድ ስጋትን አሳድሯል፤ በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ መድረክ ላይም ውግዘትን አስከትሏል።
ፕሬዚደንት ፑቲን ቀደም ሲል ማንኛውም በፕሮፌሽናል ውትድርና ያገለገለ በዩክሬይን ጦርነት ለመፋለም እንዲመዘገብ አሳስበዋል።
የፕሬዚደንቱ ጥሪ በሩሲያና ዩክሬይን መካከል ወታደራዊ ግጭት ከተቀሰቀሰ ወርሃ ፌብሪዋሪ ወዲህ ይህ ዓይነቱ የክተት ጥሪ የመጀመሪያ ነው።
የአውስትራሊያ የውጭ ጉዳዮችና ንግድ ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ትናንት ረቡዕ የፕሬዚደንቱን የክተት ጥሪ "በእጅጉ አሳሳቢ" ሲሉ ገልጠውታል።
አክለውም "ሩስያ በአስቸኳይ ዩክሬይንን ለቅቃ እንድትወጣና በዩክሬይን ሕዝብ ላይ የምታካሂደውን ኢ - ሕጋዊና ኢ - ሞራላዊ ጥቃት እንድትገታ" ሲሉም አሳስበዋል።
የጀርመን ቻንስለር ኦላፍ ሹልዝ ፕሬዚደንት ፑቲን የዩክሬይንን ሕዝብ በተሳሳተ ሁኔታ አሳንሰው ተመልክተዋል፤ የድርጊታቸው አስባብም ከጭንቀትና ጥበት የመነጨ ሲሉ ተችተዋል።
ሆኖም ከሁሉም በላይ አሳሳቢ ሆኖ የተመለከተው ፕሬዚደንት ፑቲን የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት በሩስያ ላይ የኑክሊየር ጦር መሳሪያዎችን ለመጠቀም ዕሳቤ ያለው መሆኑን አንስተው "የተወሰኑ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ከፍተኛ ተወካዮች ሩሲያ ላይ የኑክሊየር ጦር መሳሪያዎችን ስለመጠቀም" እየተናገሩ መሆኑን መግለጣቸውና "ሩስያን አስመልክተው እንዲህ ያለ መግለጫ ለመስጠት የፈቀዱትን ላሳስብ የምሻው አገራችን በተወሰኑ ዘርፎች ከቃል ኪዳኑ አገራት የዘመኑ የተለያዩ መጠነ ሰፊ አውዳሚ መሳሪያዎች እንዳሏት ነው። የአገራችን ግዛትና ክብር ለስጋት ከተዳረገ ያለ ምንም ጥያቄ ሩስያንና ሕዝባችንን ለመጠበቅ ማናቸውንም ዓይነት መንገዶች ሁሉ እንጠቀማለን። ይህ ቧልት አይደለም" ማለታቸው ነው።
ይህንኑ የፕሬዚደንት ፑቲንን ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ አስመልክቶ በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግራቸውን ያስደመጡት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን "በኑክሊየር ጦርነት ድል የለም፤ በጭራሽ ፍልሚያ ሊገጠምበትም አይገባም" በማለት የሚያስከትለውን የአጥፍቶ መጥፋት አደጋ በማመለከት የአፀፋ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጥተዋል።
ፕሬዚደንት ባይደን አክለውም፤ ለዩክሬይን ሰብዓዊ ረድኤትና የምግብ ዋስትና የሚውል $2.9 ቢሊየን መቸራቸውን ገልጠዋል።