የቪክቶሪያ መንግሥት ከትናንት ረቡዕ ጁላይ 22 ከምሽቱ 11.59 pm ጀምሮ የሜልበርንና ሚችል ሻየር ነዋሪዎች ጭምብል አጥልቀው እንዲንቀሳቀሱ የደነገገው ድንጋጌ ግብር ላይ ውሏል።
ድንጋጌውን ተላልፈው ጭምብል ሳያጠልቁ ከቤታቸው የሚወጡ ሰዎች ላይ ፖሊስ $200 መቀጮ ይጥላል።
የሜልበርን ነዋሪዎችም ድንጋጌውን ተከትለው ጭምብል አጥልቀው መንቀሳቀስ ጀምረዋል።

ሜልበርናውያን በተዋዛ መልዕክታቸው በክርስቲን ቪስባል ተቀርጻ ሜልበርን ፌዴሬሽን አደባባይ የቆመችውን "Fearless Girl" ሳይቀር ጭምብል አጥልቀውላታል።

የሜልበርንና ሚችል ሻየር ነዋሪዎች ጭምብል ሳያጠልቁ መንቀሳቀስ የሚችሉባቸው አስባቦች እንዳሉም መንግሥት ገለጧል።
እነሱም፤ በሕክምና ምክንያት፣ ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች፣ ለአካላዊ እንቅስቃሴ ሩጫ በሚደረግበት ወቅት (ከሩጫ በፊትና በኋላ ጭምብል መልበስ ግድ ይላል) ናቸው።
ትምህርት ቤቶች ውስጥ መምህራን በሚያስተምሩበት ወቅት ጭምብል ማጥለቅ ግድ አይሰኙም።
ሆኖም ከ11ኛ እስከ 12ኛ ክፍልና የ VCE እና VCAL ተማሪ የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች ጭምብል ማጥለቅ ይጠበቅባቸዋል።
ፈቃድ ባለው ጉዳይ ወደ ሜልበርናን ሚችል ሻየር የሚዘልቁ የገጠር አካባቢ ነዋሪዎች በእንቅስቃሴያቸው ወቅት ጭምብል የመልበስ ግዴታ አለባቸው።

